AMN – ጥር 29/2018 ዓ.ም
48 ኪ.ሜ ሜትር ዝርመት የሚሸፍኑ 8 የወንዝ ዳርቻ ልማቶች እየተከናወኑ መሆናቸዉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤዉን በአድዋ ድል መታሰቢያ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ አበባ አሁን ላይ በተከናወኑና እየተከናወኑ ባሉ የኮሪደር እና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ከተማዋ ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪነቷን የሚያሳድግና ገፅታዋን የቀየረ ለነዋሪዎችና ለቱሪስቶችም ቀልብ ማረፊያ እና ተመራጭ እንድትሆን አስችሏታል ፡፡

በሪፖርታቸውም ባለፉት ስድስት ወራት የአራት ኪሎ – ሽሮ ሜዳ፣ የሳውዝጌት – መገናኛ – መስቀል አደባባይ ፣ የሳርቤት – ካርል አደባባይ – አቦ ማዞሪያ – ላፍቶ አደባባይ – ፉሪ ፣ የሲኤምሲ -ሰሚት- ጎሮ – ቦሌ ቪአይፒ ኮሪደር ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት ክፍት መሆናቸውን አንስተዋል ፡፡
በከተማዋ 3ሺህ ሄክታር መሬትና 48 ኪ.ሜ ሜትር ዝርመት የሚሸፍኑ 8 የወንዝ ዳርቻ ልማቶች እየተከናወኑ መሆኑንም ነው ከንቲባዋ የጠቀሱት ፡፡
በተለይም 25 ኪ.ሜ በላይ የሚሸፍነው የእንጦጦ ፒኮክ-ካራማራ ድልድይ፣ 2ዐ ኪ.ሜ የሚሸፍነው የቀበና ግንፍሌ እንዲሁም ቁርጡሚ ወንዝ ዳርቻ እጅግ ውብ፣ ጤናማ አየር የሚተነፈስባቸው የቱሪስት መዳረሻ ሆነው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል፡፡
ከነዚህ በተጨማሪ አራዳ ፓርክ፣ አራት ኪሎ መኪና ማቆያና የገበያ ማእከል፣ የአራዳ የመኪና ማቆሚያ እና የገበያ ማዕከል እንዲሁም የመኪና ማቆሚያና የድል ፕላዛ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተናገሩት ፡፡
በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎቸን ቀጣይነት ለማረጋገጥ መዋቅር በማዘጋጀት የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ባለስልጣን በማቋቋም ወደ ስራ መገባቱንም ከንቲባዋ ገልፀዋል ፡፡
በያለው ጌታነህ