AMN- ጥር 29/2018 ዓ.ም
ከንቲባዋ ባቀረቡት የከተማ አስተዳደሩ የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የከተማዋን ምቾትና ደኅንነት ለመጠበቅ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
በከተማዋ በተከናወነው ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን የመግታት ዘመቻም፣ የከተማዋን ሰላማዊ እንቅስቃሴና ውበት ለማስጠበቅ የተቀናጀ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ፣ የጎዳና ላይ ንግድ፣ሕገ-ወጥ እርድና ማስታወቂያዎችን በመከላከል ረገድ ትልቅ ውጤት ተመዝግቧል።
አዋኪ ድርጊቶችና ሕገ-ወጥ የደረቅና ፍሳሽ አወጋገድ ስርዓቶችን በመቆጣጠር የከተማዋን ምቾት የመጠበቅ ሥራም መሠራቱን ተናግረዋል።

የወንጀል ምጣኔ ከመቀነስ አኳያም ከሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ከሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ከዝርፊያ እና ደረቅ ወንጀሎች ጋር የተያያዙ በርካታ እርምጃዎች የመውሰድ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡
በፍትሕ ሥርዓቱም የሕግ የበላይነትን በማስከበር የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲጎለብት ለማድረግ በርካታ ተግባሮች መከናወናቸውን ነው ያመለከቱት።
የአቃቤ ሕግን አቅም በማሳደግ ረገድ በተከናወኑ ሥራዎች፣ በአስተዳደሩና በነዋሪው መብት ላይ ከፍተኛ ድል ተመዝግቧል ያሉት ከንቲባዋ፣ በፍርድ ቤት ክርክር ከነበሩ 1 ሺህ 491 መዝገቦች ውስጥ 1 ሺህ 382ቱን ለአስተዳደሩ በማስወሰን ከ3 ቢሊየን ብር በላይ የመንግስትና የሕዝብ ሀብት ከምዝበራ መታደግ መቻሉን ተናግረዋል።
ከንብረት ጥበቃ አኳያም፡ በአይነት 101 ቤቶች፣ 19 ሼዶች እና 178 ሔክታር መሬት ሕጋዊነታቸው ተረጋግጦ እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።
በታምራት ቢሻው