በግብር ከፋዩ ላይ የግብር መጠን የመጨመር ዕቅድ የለንም – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በግብር ከፋዩ ላይ የግብር መጠን የመጨመር ዕቅድ የለንም – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ጥር 29/2018 ዓ.ም.

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አስመልክቶ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በግብር ከፋዩ ላይ ግብር የመጨመር ሐሳብ የሌለው መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፥ ይልቁንም የገቢ መሠረትን በማስፋትና ፍትሐዊነትን በማስፈን ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የገቢ አሰባሰብ ሒደቱን ለማስቀጠል የገቢዎች ቢሮን በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በአሠራር የማጠናከር ሥራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተማዋ ገቢ ለማመንጨት ካላት አቅም አኳያ አሁን እየተሰበሰበ ያለው ገቢ በቂ አለመሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች፥ ያልተደረሰባቸውን የገቢ ማስገኛ መንገዶች ወደ ግብር ሥርዓቱ ለማስገባት በሳይንሳዊ መንገድ ጥናት እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

ከዚህ በፊት የማይሰበሰቡ ገቢዎች ተደርሶባቸው ግብር መሰብሰብ ሲጀመር ግብር ተጨመረብን የሚሉ ድምጾች ሊሰሙ ይችላሉ ያሉት ከንቲባዋ፥ እነዚህ ድምጾች ግን እውነተኛ እንዳልሆኑና ሕዝቡ ሊረዳቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከተማዋ በራሷ ገቢ የምትተዳደር እንደመሆኗ መጠን፣ የገቢ መሠረትን የማስፋትና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review