“በሜጋ ፕሮጀክት አመራር፣ ክትትል እና አፈጻጸም ገና ድፍን አፍሪካ ከኢትዮጵያ ይማራል”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላትን ቦታ የበለጠ ከፍ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል
ዓባይ ውሃ ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያስተሳሰረ ከደም የወፈረ ሰንሰለት እንጂ። አዎ ዓባይ፣ በከፍተኛ ጥበብ፣ ብርታትና ትብብር በአለት ላይ የፀና የውሃ ሐውልት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ከፍታ፣ ጥበብና ፅናት ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይቀዳል፡፡
ለአብነትም ግድቡ በምጣኔ ሀብት እሳቤ ሲመዘን እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አህጉር ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ሞራል፣ ለመፈፀምም ስንቅ እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አንዱዓለም ባዩ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
ለዚህም ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ የታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን መሆኑን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከግድቡ መጠናቀቅ ባሻገር ይፋ ያደረጓቸውን የኒውክሌር ማበልጸጊያ፣ የጋዝ ፋብሪካ ማስመረቅ፣ የነዳጅ ማጣሪያ እውን ማድረግ፣ በአፍሪካ ግዙፉ አየር ማረፊያ፣ 2ኛውን የጋዝ ፋብሪካ ግንባታ እና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ማስጀመርን (የጉባ ብስራቶችን) በዋቢነት ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ እንደ አህጉርም ሆነ እንደዓለም ያላትን ከፍታና ተደማጭነት የበለጠ የሚያፀኑና ሁለንተናዊ ኃያልነቷን የሚያረጋግጡ መሆናቸውንም የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አንዱዓለም (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ማክሰኞ 6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ “በሜጋ ፕሮጀክት አመራር፣ ክትትል እና አፈጻጸም ገና ድፍን አፍሪካ ከኢትዮጵያ ይማራል” ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ዜጎች በዋጋ ግሽበት ሳቢያ የሚደርስባቸውን ጫና በመግታት ኢኮኖሚውን የማጠንከር ጉልህ ሚና አለው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አንዱዓለም (ዶ/ር) የነዳጅ ዋጋ ወጥ ያለመሆን የኑሮ ውድነትን የሚያባብስ መሆኑን በመግለፅ የጋዝ ማምረቻ ፋብሪካው ለዚህ ምላሽ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለም መሬት ያላት እና ለግብርና ዘርፍ የተመቸች ብትሆንም በሚገባት ልክ ተጠቃሚ እንዳትሆን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ዋነኛ ማነቆ እንደሆነ የገለፁት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ ሆኖም በእቅዷ የተካተተውና ወደ ተግባራዊ ምእራፍ የተሸጋገረው የማዳበሪያ ማምረቻ ፕሮጀክት ከራስ ባለፈ ለሌሎች ሀገራት ማቅረብ የሚያስችል እና ለአፍሪካ ጭምር ተጨማሪ ገጸበረከት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ግዙፉ የአውሮፕላን ማረፊያ እና የዜጎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ እየተሄደበት ያለ ሌላ ትልቁ እመርታ እንደሆነ የተናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ ጉባ ላይ የተበሰሩት ታላላቅ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ መጭው ዘመን ብርሃናማ መሆኑን አመላካች ናቸውም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በራስ አቅም መቆም የቻለች ሀገር የሚገጥማትን ዓለም አቀፋዊ ጫና የመመከት አቅሟ የጎለበተ ነው የሚሉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ባለሙያ ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) አለማችንን እንዳሻቸው የሚዘውሩ ሀገራት የኃይል ምንጫቸው የኢኮኖሚ ከፍታቸው ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ታዲያ 7ቱ የጉባ ብስራቶች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ በቀጣናውም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን የኢኮኖሚ አቅም የሚያጠናክሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አንዱዓለም ባዩ (ዶ/ር) እንደሚሉት የኒውክሌር ፕሮጀክቱ እና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ሀገሪቱ በኃይል አቅርቦት ያላትን አቅም ያሳድጋሉ፣ ኢንቨስትመንት ይስባሉ፣ የውጭ ምንዛሬንም ያሳድጋል፤ የእነዚህ ድምር ውጤትም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በፅኑ መሰረት ላይ በማንበር ሁለንተናዊ ተደማጭነቷንና ከፍታዋን ይጨምራሉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምራ እየጨረሰች መሆኑን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሳይታለች የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ በጉባ የተበሰሩትን ታላላቅ ፕሮጀክቶችንም እውን መሆን የመሰረተ ልማትን ከማስፋፋት፣ ሰፋፊ የስራ ዕድልን ከመፍጠር፣ የዜጎችን ኑሮ የበለጠ ከማሻሻል ባሻገር ኢትዮጵያ በመጭው ዘመን እንደ አህጉርም ሆነ እንደ ዓለም የበለጠ ማንፀባረቋ አይቀሬ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ባሳለፍነው ሕዳር ወር መጨረሻ ‘የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች’ በሚል መሪ ሃሳብ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሕዝባዊ የውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚሁ ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የጉባ ብስራት ግዙፍ ፕሮጀክቶች የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ልዕልና ለማረጋገጥ እንደሚተጋ ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ ኃይል ለአንድ ሀገር እድገት፣ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ እና የኑሮ ደረጃዎች መሻሻል መሠረት ነው የሚሉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ይንገስ ዓለሙ (ዶ/ር) ለአብነትም በታሪክ፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገሮች በመሠረተ ልማት፣ በትምህርት፣ በጤና አጠባበቅ እና በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የተሻለ ቦታ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ዓለም የምትንቀሳቀሰው በኢኮኖሚ ሞተርነት ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገሮች በዓለም ፖለቲካ፣ በንግድ፣ ብድርና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ውሳኔዎችን እስከ መምራት የደረሰ ተፅዕኖ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
የታሪክ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ፕሮፌሰር ፖል ኬኔዲ “The Rise and fall of the Great Powers” በተሰኘ መፅሀፋቸው ላይ እንደጠቀሱት የሀገር መውደቅና መነሳት ዋና ምስጢሩ ኢኮኖሚ ነው፡፡ በመሆኑም “7ቱ የጉባ ብስራቶች” የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በአስተማማኝ መሰረት ላይ የሚገነቡና የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ከፍታ የሚዘውሮ ሞተሮች እንደሚሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አንዱዓለም ባዩ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
ለአብነትም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በጉባ ይፋ ካደረጓቸው ብስራቶች መካከል በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የአየር ማረፊያ ግንባታ ይጠቀሳል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፍያ ግንባታ ስራ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ባደረጉት ንግግርም፣ የአየር ማረፊያ ግንባታው የኢትዮጵያ የዝመና ጉዞ፣ የብልፅግና፣ የመለወጥ፣ ራሷን ችላ በሁለት እግሯ የመቆም መሻትን የሚገልጥ ስራ እንደሆነ መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡
በፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ 60 ሚሊዮን መንገዶችን ማስተናገድ የሚችል የአየር ማረፊያ ግንባታ በፈረንጆች አቆጣጠር 2030 ይመረቃል፡፡ በሁለት ምዕራፎች የሚገነባው የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እና ሌሎች የተጀመሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሲጠናቀቁ ከአስር ዓመት በኋላ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2036 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ ኢኮኖሚ ትገነባለች ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፡፡
የኢትዮጵያ ጥንታዊ ትሩፋት እና በአፍሪካ ዘመናዊ ልማት ላይ ያላት ሚና ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ የህዳሴው ግድብ አንዱ ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንታዊ መንግሥቶቿ ጀምሮ እስከ አሁን ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች የአፍሪካን የታሪክ ሂደት ባማረ መልኩ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና መጫዎቱን የታሪክ ድርሳናት ምስክር ናቸው፡፡
በተለይ ጉባ ላይ የተበሰሩ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የጋዝ ፋብሪካዎች፣ ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኒውክሌር ጣቢያ የመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላትን ቦታ የበለጠ ከፍ እንደሚያደርጉ ከዝግጅት ክፍላችን ጋ ቆይታ ያደረጉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ