በጊዜው አማረ
አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥን ተግባር እየከወነች ትገኛለች፡፡ ያለፉት ጥቂት ዓመታት ክንውኗም ይህን በግልፅ ያመላክታል፡፡ ተግባራቱ ገጽታን የሚገነቡ፣ የገቢ አቅምን የሚያሳድጉ፣ ከምንም በላይ ደግሞ ሰው ተኮር መሆናቸው ፋይዳቸውን የገዘፈ ያደርገዋል፡፡ ለዚህ አስረጂ ይሆን ዘንድ ትናንት በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ያቀረቡትን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም በሚከተለው መልክ አቅርበነዋል፡፡
ፓለቲካ ዘርፍ
ሰላም፣ ፀጥታና ፍትህ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፓርታቸው እንደገለጹት፣ ከ22 ሺህ በላይ አዳዲስ የሰላም ሰራዊት በመመልመልና በማሰልጠን ለጸጥታ ስራው አጋዥ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል፡፡ የሰላም ሰራዊት አባላት ከጸጥታ ሃይል ጋር የተቀናጀ ስምሪት በመውሰድ፣ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ተደርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ የሚስተዋሉ የደንብ መተላለፎችንና ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ተፈፅሞም ሲገኝ ማረም እንዲቻል ብቁ፣ በስነ ምግባር የታነጹ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮችን በ9 ዙሮች በማሰልጠን የተለያዩ የደንብ መተላለፎችን በመከላከል ረገድ አበረታች ስራ አከናውነዋል፡፡
አገልግሎት አሰጣጥ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማብራሪያቸው እንደገለጹት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በተሰራው ስራ 23 አዳዲስ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የተደገፉ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ አሁን ላይ በአጠቃላይ 370 አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ታግዘው እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል፡፡
በተለይም ሁለት አዳዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት መስጫዎች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲለሙ በማድረግ፣ ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ማድረግ በመቻሉ የተገልጋዩን ህብረተሰብ እንግልት፣ ጊዜንና ወጪን መቀነስ፣ እርካታውንም 94 ነጥብ 2 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን በመጠቀም በአገልጋዩ፣ በዋርካ፣ በምርመራ ጋዜጠኝነት ስራ እና በሌሎች ፕሮግራሞች ህዝቡ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ሃሳብ የሚያነሳበት፣ መንግስትም የሚነሱ ጥያቄዎችን ለቅሞ የሚፈታበት ስርዓት መፍጠር ተችሏል። በሂደቱም በርካታ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡
ማህበራዊ ዘርፍ
ትምህርት
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፓርታቸው፣ የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለትምህርት ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ባደረገው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ከተማሪዎች ውጤት አንጻር የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች 2015 ዓ.ም ከነበረበት 80 ነጥብ 2 በመቶ በአሁን ወቅት 95 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ከ50 በመቶ በላይ የሚያመጡ ተማሪዎች በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 36 ነጥብ 1 በመቶ በአሁን ወቅት 88 ነጥብ 8 በመቶ ደርሷል፡፡ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች 2013 ዓ.ም ከነበረበት 25 ነጥብ 45 በመቶ በአሁን ወቅት 31 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በተማሪዎች ምገባ ከ940 ሺህ 329 በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ እንዲመገቡ እየተደረገ ሲሆን፣ የተማሪ ዩኒፎርም፣ የትምህርት ቁሳቁስ እና የመምህራን ጋወን በወቅቱ ማድረስ መቻሉን አክለዋል፡፡
ጤና
የእናቶች፣ የጨቅላ ህጻናት እና የድንገተኛ፤ የአስተኝቶ ህክምና እና ጽኑ ህሙማን ሞት ምጣኔ በሁሉም መለኪያዎች ከእቅድ በላይ መከናወኑን የገለጹት ከንቲባዋ፣ በእነዚህ መለኪያዎች በ2030 በዘላቂ ልማት ግቦች በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት እንዲያሳኩ የተያዙ የጤናው ዘርፍ ኢላማዎችን ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
አክለውም የኤሌክትሮኒክ የጤና መረጃ አያያዝ ስርዓትን (EMR) ወረቀት አልባ ያደረጉ ተቋማትን በእቅድ ከ57 ወደ 63 ለማድረስ ታቅዶ ሁሉንም ሆስፒታሎች ጨምሮ በአጠቃላይ በ67 (117 በመቶ) ጤና ተቋማት ከእቅድ በላይ መከወን መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎትን ከማጠናከር አንጻር፣ የከተማ አስተዳደሩ ለፕሮግራሙ በየዓመቱ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ የአባላትንም ሽፋን ከማሳደግ አንጻር አምና ከነበረው 2 ነጥብ 57 ሚሊዮን አጠቃላይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን የሚችል ማህበረሰብ ቁጥር ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ማሳደግ መቻሉንም አብራርተዋል፡፡
“የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን የያዝነውን ራዕይ ለማሳካት ከ500 በላይ አልጋ የሚኖራቸው የኮልፌ መንዲዳ እና የንፋስ ስልክ ላፍቶ ሁለት ግዙፍ ዘመናዊ ሆስፒታሎች እንዲሁም በሀገራችን በአይነቱ የመጀመሪያ፣ ልዩ እና ከ511 በላይ አልጋዎች የሚኖሩት የገላን ትራውማ ሆስፒታልን (Gelan Trauma Hospital) ጨምሮ በአጠቃላይ ሶስት አዲስ ሆስፒታሎች ግንባታቸው ተጠናቅቆ የሕክምና መሳሪያዎችን ለማሟላት ዝግጁ እየተደረጉ ይገኛል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢኮኖሚ ዘርፍ
ቱሪዝም
ከንቲባዋ በሪፖርታቸው እንደገለጹት፣ ባለፉት ስድስት ወራት ከተማዋን ይጎበኛሉ ተብሎ ከታቀዱ 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን (104 በመቶ) መጎብኘት ችለዋል፡፡ ለዚህ ሲከበሩ የነበሩት ህዝባዊ፣ ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ የአደባባይ በዓላት እንዲሁም የስፖርትና የጤና ቱሪዝም መስፋፋት ከፍተኛ አበርክቶ ነበራቸው ብለዋል፡፡
“ባለፉት ስድት ወራት 150 የሚሆኑ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ኩነቶች አዲስ አበባ ላይ ተካሂደዋል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ50 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት በአጠቃላይ ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ከውጪ ሀገር የቱሪስት ፍሰት 155 ቢሊዮን ብር ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ ማድረግ ተችሏል” ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
የስራ እድል ፈጠራ
ከንቲባ አዳነች፣ የስራ ስምሪት አገልግሎትን በማስፋፋት ለስራ ፈላጊ ዜጎች ዘለቄታዊ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር እና የምግብ ዋስትና እጦት ተጋላጭነትን በመከላከል ድህነትን በመቀነስ ረገድ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ለ178 ሺህ 500 ነዋሪዎችን የሥራ ዕድል ለመፍጠር በዕቅድ የተያዘ ሲሆን 195 ሺህ 112 (109 በመቶ) ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ለምክር ቤቱ አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም በኮሪደር ስራና በቤቶች ግንባታ ከ250 ሺህ በላይ ሰዎች ጊዜያዊ የስራ እድል ተፈጥሮላቸው በግንባታው ላይ እየሰሩ ነው፡፡ የተፈጠረው የስራ እድልም በከተማ ግብርና 15 ሺህ 695 (8 በመቶ)፣ በኢንዱስትሪ 41 ሺህ 663 (21 በመቶ) እና በአገልግሎት ዘርፍ 137 ሺህ 754 (71 በመቶ) ሽፋን ይዘዋል። በዚህም ከተጠቃሚነት አንጻር ሴቶች 53 ነጥብ 7 በመቶ፣ ወጣቶች 49 ነጥብ 25 በመቶ እና ምሩቃን 13 ሺህ 179 (6 ነጥብ 8 በመቶ) ድርሻ መያዛቸውን አክለዋል፡፡
መሬት
እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፣ የኦንላይን አገልግሎትን በማሳለጥ ባለፉት ስድስት ወራት 13 ሺህ 669 ካርታዎች ታትመው እንዲሠራጩ ተደርጓል ያሉት ከንቲባዋ፣ ከዚህ ውስጥ በተሻሻለው ሲስተም 10 ሺህ 528 ካርታዎች ታትመው እንዲሰራጩ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለተለያዩ አገልግሎቶች 341 ሄክታር መሬት ለማዘጋጀት ታቅዶ 465 ነጥብ 42 ሄክታር (ከ100 በመቶ በላይ ) ማዘጋጀት ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉና የከተማዋን ፍላጎት መሠረት ያደረገ 294 ነጥብ 20 ሄክታር መሬት ለማስተላለፍ ታቅዶ 483 ነጥብ 45 (ከ100 በመቶ በላይ) ሄክታር ማስተላለፍ ተችሏል፡፡ የቅድመ ማልማት ጥያቄ ላቀረቡ 54 ባለይዞታዎች በይዞታቸው ላይ ማልማት እንዲችሉ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ለልማት ተነሺዎች 7 ነጥብ 35 ቢሊዮን ብር ካሣ መክፈል የተቻለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በልማት ምክንያት ለተነሱት ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ (ለመብራት) አገልግሎት ከ 400 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ተፈጽሟል፡፡
እንዲሁም የአርሶ አደር መብት ፈጠራ አፈፃፀምን በሚመለከት 6 ሺህ 122 ካርታዎች የታተሙ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ 10 ሺህ 873 ታትመው አርሶ አደሩ እጅ እንዲደርሱ ተደርጓል። ለ50 አርሶ አደሮች በይዞታቸው ላይ እንዲያለሙ ውሳኔ ተሰጥቶ ወደ ልማት እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል፡፡ 41 ሺህ 454 ይዞታዎች ለመመዝገብ ዕቅድ ተይዞ 34 ሺህ 802 (83 ነጥብ 9 በመቶ) ተከናውኗል፡፡ የመብት ምዝገባና የመስክ አገልግሎት ጥያቄዎችን በተመለከተ ለ84 ሺህ 996 ተገልጋዮች ምላሽ ለመስጠት ታቅዶ ለ94 ሺህ 927 ማሳካት መቻሉን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡
የኮሪደር እና ወንዝ ዳርቻ ልማት
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማብራሪያቸው፣ “ከኮሪደር እና ወንዝ ዳርቻ ልማት አንጻር በመተግበር ላይ የነበሩ የአራት ኪሎ-ሽሮ ሜዳ፣ የሳውዝጌት-መገናኛ – መስቀል አደባባይ፣ የሳርቤት-ካርል አደባባይ-አቦ ማዞሪያ-ላፍቶ አደባባይ-ፉሪ እና የሲኤምሲ-ሰሚት-ጎሮ-ቦሌ ቪአይፒ ኮሪደሮች ተጠናቅቀው ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ሆነዋል፡፡
በተጨማሪም 3 ሺህ ሄክታር መሬትና 48 ኪሎ ሜትር ዝርመት የሚሸፍኑ 8 የወንዝ ዳርቻ ልማቶች እየተከናወኑ ነው፡፡ በተለይም 25 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍነው የእንጦጦ ፒኮክ-ካራማራ ድልድይ፣ 2ዐ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የቀበና ግንፍሌ እንዲሁም ቁርጡሚ ወንዝ ዳርቻ እጅግ ውብ፣ ጤናማ አየር የሚተነፈስባቸው የቱሪስት መዳረሻ ሆነው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ አራዳ ፓርክ፣ አራት ኪሎ መኪና ማቆያና የገበያ ማእከል፣ የአራዳ የመኪና ማቆሚያ እና የገበያ ማዕከል እንዲሁም የመኪና ማቆሚያና የድል ፕላዛ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል” ያሉ ሲሆን የተሰሩትን ቁልፍ የሆኑ መሰረታዊ ልማቶች ከማስቀጠል አንፃር መዋቅር በማዘጋጀት የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ባለስልጣን ተቋቁሞ ወደ ስራ የተገባውም በዚሁ ግማሽ ዓመት መሆኑን ገልጸዋል:: ከንቲባዋ እየተሰሩ ያሉትን የኮሪደር ልማቶች ከማገናኘት አንጻር ከኡራኤል-አትላስ-ቦሌ ብራስ፣ ከጎላጎል-ኤድናሞል-ፍሬንድሺፕ እና ከውሃ ልማት በአትላስ ሩዋንዳ ድልድይ ኮሪደሮች እየተገባደዱ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ ባለፉት 6 ወራት ብቻ በመደበኛ እቅዶች ከተከናወኑት በተጨማሪ በኮሪደር ልማት 17 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ 34 ኪሎ ሜትር የእግራኛ መንገድ እና 13 የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡