“ሀገሬን ወክዬ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ጉባኤ ላይ ስካፈል በጣም አፍር ነበር”

You are currently viewing “ሀገሬን ወክዬ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ጉባኤ ላይ ስካፈል በጣም አፍር ነበር”

                                                                                                                                                                            አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና

መንግስት የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እየሄደበት ያለው መንገድ የሚደነቅ መሆኑ ተጠቁሟል

ሀገራት ያላቸው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ከባህር ጋር ያላቸው ግንኙነት በዓለም ፖለቲካ ላይ የሚጫወቱትን ሚና ይወስነዋል፡፡ ታዋቂው አሜሪካዊ ጋዜጠኛና ደራሲ ሮበርት ካፕላን “The Revenge of Geography” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚገልፁት በአውሮፓና አፍሪካ መካከል ያለው ትልቅ መልክዓምድራዊ ልዩነት የባህር በር ከማግኘት ጋር የተያያዘ ነው፡፡

አውሮፓ የቆዳ ስፋቷ ትንሽ ቢሆንም ከስፋቷ አንፃር ሰፊ የባህር በር ስላላት የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማድረግና በዓለም ላይ ዘመናዊ ኢኮኖሚ በመገንባት ፈርቀዳጅ ለመሆን ችላለች፡፡ አፍሪካ በተቃራኒው ሰፊ የቆዳ ስፋት ቢኖራትም ከስፋቷ አንፃር ያላት የባህር በር አነስተኛ መሆኑ በከፊል ከዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንድትገለልና እስከአሁንም በድህነት ውስጥ እንድትኖር አድርጓታል ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ባሳለፈችው ረጅም ታሪክ ውስጥ ስልጣኔና እድገቷ ከባህር ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የባህር በር በነበራት ጊዜ በተሻለ ሁኔታ የንግድ ልውውጥ ማካሄድ፣ ህልውናዋን ማስጠበቅና ተፅዕኖ መፍጠር ችላለች፡፡ ኢትዮጵያ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ የቀይ ባህር አዋሳኝ ሀገር ስለነበረች ማንኛውም በባህሩ ላይና ከዚያ ጋር ተያይዞ የሚነሳ እንቅስቃሴን በቅርበት የመቆጣጠርና የመከታተል ስልታዊ ጠቀሜታ አግኝታ ነበር፡፡ ይህንን ጠቀሜታ ግን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተለየች በኋላ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ባለፉት ዓመታት አጥታዋለች። የባህር ማጣቷ የፖለቲካና ደህንነት፣ ስትራቴጂካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ተያያዥ ጉዳቶች ተጋላጭ እንዳደረጋት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የተዘጋጀው “የሁለት ውኃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ” ሰነድ ላይ የሰፈረው መረጃ ያሳያል፡፡

ኢትዮጵያ በአካባቢው ካሉ ሀገራት በህዝብ ቁጥር፣ በወታደራዊ ሃይል ሚዛንና በኢኮኖሚ እድገት በአንፃራዊነት የተሻለች ብትሆንም የባህር በር የሌላት በመሆኑ በቀጣናው ልትጫወት የምትችለውን ሚና አቀጭጮታል፡፡ ከኢኮኖሚ አኳያ ለከፍተኛ ወጪ ዳርጓታል፡፡ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን በ2016 ዓ.ም በገፀ ድሩ ላይ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ በዓመት ለወደብ ኪራይ ክፍያ እስከ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ታወጣለች፡፡

ኢትዮጵያ ባህር አልባ ሀገር በመሆኗ ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ ነው፤ በአጭሩ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት እንዳለባት በአንዳንድ የሀገር ተቋርቋሪ ወገኖች ጥያቄ ሲነሳ የነበረ ቢሆንም፤ “የኤርትራን ሉዓላዊነት የሚጋፋና የተስፋፊዎች አጀንዳ” በሚል ውድቅ ይደረግ ነበር። በመንግስት ደረጃ የተዘጋ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሁለት ዓመት በፊት የባህር በር ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ማንሳታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ ትኩረት እየሳበ መጥቷል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በተለያየ ኃላፊነት ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ያገለገሉት አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፣ ለኢትዮጵያ የአሁኑም ሆነ መጪው ትውልድ የባህር በር በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ሀገሪቱ አሁን እያስመዘገበችው ባለው የኢኮኖሚ እድገት ከቀጠለች በርግጠኝነት በቅርብ ጊዜ የአካባቢው ሀያል ሀገር መሆን ትችላለች፡፡ ባለፉት 60 ዓመታት ገደማ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሁኔታ በቅርበት ተከታትያለሁ፤ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ለውጥ ከፍተኛ የሚባል እና ትልቅ ተስፋን የሚፈነጥቅ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ በግድብ ግንባታ፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ ጋዝ ልማት እንዲሁም ወርቅ ወደ ውጪ በመላክ ወደፊት እየመጣች ያለች ሀገር ናት፡፡ ይህንን ግዙፍ የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሸከም የሚችልም ወደብና የወደብ መሰረተ ልማት ያስፈልጋታል፡፡

ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር እያደገ ይገኛል፡፡ 130 ሚሊዮን ይገመታል፡፡ “ኢትዮጵያን ወክዬ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ጉባኤ በተለያየ ሀገራት ሲደረግ ተካፍያለሁ፤ በጣም አፍር ነበር። እንዳፍር የሚያደርገኝ ከእኛ ጋር የሚሳተፉ ሀገሮች ያላቸው በዛ ቢባል ከ20 ሚሊዮን የማይበልጥ ህዝብ ነው፡፡ እንደ እኛ ትልቅ ሀገር ሆኖ የባህር በር የሌለው በዓለም ላይ የለም” ይላሉ አምባሳደር ጥሩነህ፡፡

ምን ዓይነት አካሄዶችን መከተል ያስፈልጋል?

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ባደረገው 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ በአፍሪካ ካለው ረጅም ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባህር ጠረፍ ውስጥ ኢትዮጵያ የጠየቀችው 50 ኪሎ ሜትር ወደ ባህር መውጫ በር እንዲሰጣት ነው። ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ በመስጠት አሊያም በኪራይ (ሊዝ)፣ በመሬት ልውውጥ አማራጮች በስምምነት የባህር በር ማግኘት ትፈልጋለች፡፡ ይህንን ጉዳይ መቀበልም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ የግድ ነው፡፡ አዋጪው መንገድ ለጎረቤት ሀገራት ያለውን ሀብት በመጋራት ተያይዞ ማደግ ነው ብለዋል፡፡

“የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢ እንደሆነ፣ ነገር ግን በጦርነት መሆን እንደሌለበት ያምናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወዳጅ ሀገራትም ጥያቄው ቀርቦላቸው “ጊዜ ስጡን፤ እንምከርበት” የሚል መልካም ምላሽ እንደሰጡና በጊዜ ሂደት ፍሬ እንደሚያፈራ ተናግረዋል፡፡

አምባሳደር ጥሩነህ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ እውን እንዲሆን አንድ መንገድ ብቻ አያዋጣም፤ የተለያዩ አማራጮችን ማየትና መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ሰጥቶ መቀበል መርህ አንዱ ነው፡፡ ጥያቄውን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ግጭት እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የሌሎች ሀገራትንም ተሞክሮ ማየት ያስፈልጋል፡፡ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ማግኘት ካልተቻለ ሩስያ፤ “የእኔ ነው፤ ባለቤትነት አለኝ” የምትለውን ክሪሚያን ለማስመለስ የሄደችበትን መንገድም ማየት ያስፈልጋል።

አምባሳደር ጥሩነህ በማብራሪያቸው፣ መንግስት የባህር በርን አጀንዳ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ጥያቄ እንዲታወቅና ምላሽ እንዲያገኝ እየሄደበት ያለው መንገድ የሚደነቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ለአርባ ዓመታት ያህል በውጭ ጉዳይ ላይ በተለያየ መልኩ ሰርቻለሁ፡፡ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ያለባህር በር የኖርንበትን ሁኔታ አውቃለሁ፡፡ በእነዚያ ዓመታት የባህር በር እንዲኖረን ፍላጎት ያለው መንግስት አልነበረም፡፡ ‘አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም’ እንደሚባለው እያወቀ ነው የባህር በር ለኤርትራ የሰጠው፡፡” ብለዋል፡፡

 “የሁለት ውኃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ” ሰነድ ላይ እንደተገለፀው፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን ውስጣዊ አቅምን ማጠናከር፣ የዜጎችን የባህረኛነት ሙያና ባህል ማጎልበት፣ የትብብር እድሎችን መጠቀም (የግዛት ልውውጥ፣ ነፃ የንግድ ቀጣና፣ ኢትዮጵያን የቀጣናው የስበት ማዕከል ማድረግ)፣ የብዝሃ ሀያል የዓለም አቀፍ ፖለቲካን መጠቀም እና መሰል ስትራቴጂዎችን መከተል ያስፈልጋል። እንዲሁም ልዩ ልዩና አግባብነት ያላቸው ኢ-መደበኛ አማራጮችን እንደአስፈላጊነቱ መጠቀም ያስፈልጋል። ይህም ሲባል ምቹ ጊዜና ሁኔታ ሲፈጠር አማራጮችን ሁሉ ለመጠቀም አስቀድሞ መዘጋጀትና አቅምን ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ኮሶቮ ነፃ ሀገር የሆነችበት ሂደት፣ እስራኤል የሶርያ ግዛት የሆኑትን የጎላን ኮረብታዎች በሀይል ይዛ ከሀምሳ ዓመት በላይ የቀጠለችበት፣ ሩስያ ክሪሚያን የጠቀለለችበትን መንገድ ማየት ያስፈልጋል፡፡

“የባህር በር ጥያቄው እውን እንዲሆን ምሁራን፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ህዝቡ ከመንግስት ጎን አብረው በመቆም መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ይጠበቃል፡፡ መንግስት ባለፉት ሃያ ወይም ሰላሳ ዓመታት ያልተሰሩ ስራዎችን በጥቂት ጊዜ ሰርቶ እያሳየ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ሀገርን ወደኋላ ለመመለስ የሚሰሩ አካላት አሉ፡፡ እነዚህን ከመንግስትና ህዝብ ጋር አብረው እንዲቆሙ ማሳመን ያስፈልጋል። ከመንግስት ባሻገር ሁሉም ባለው አቅም የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀት ይኖርበታል” ሲሉ አምባሳደር ጥሩነህ ተናግረዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review