የተተኪ ስፖርተኞች መፍለቂያ ምንጮች

You are currently viewing የተተኪ ስፖርተኞች መፍለቂያ ምንጮች

ትምህርት ቤቶች የዕውቀት ገበታ ብቻ ሳይሆን የነገው ስብዕና የሚታነጽበት የታላላቅ ህልሞች መፈልፈያ ጣቢያዎች ናቸው ማለት ይቻላል። እንደዚሁም ተሰጥኦ የሚለይባቸው፣ ስነ ምግባር የሚታነጽባቸው እና ህልሞች ክንፍ የሚያወጡበት ስፍራ ናቸው ትምህርት ቤቶች። የተማሪዎች ውጤታማነትም የሚለካው በፅንሰ ሀሳብ እውቀት ብቻ ሳይሆን በስፖርታዊ ሜዳዎች ላይ በሚያሳዩት ልዩ ልዩ ተሰጥኦ፣ በቡድን ስራ መንፈሳቸውና በአካላዊ ጥንካሬያቸውም ጭምር ነው።

ዛሬ ላይ ስፖርት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለው ሚና ከጨዋታነት አልፎ ወደ ስነ-ልቦናዊ ልህቀትና ወደ ማህበራዊ ትስስር ተሸጋግሯል። ይህንን የተገነዘበው የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደርም ለ2ኛ ጊዜ ከተማ አቀፍ የተማሪዎች ስፖርት ሊግ እና የመምህራን ስፖርታዊ ውድድር ማካሄድ ጀምሯል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ ትምህርት ቤቶችና ስፖርት ያላቸውን ቁርኝት፣ ከትምህር ቤት ተነስተው ስኬታማ ስለሆኑ ስፖርተኞችና ስፖርቱ በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ ስለሚፈጥረው ተፅዕኖና መሰል ጉዳዮችን  እንቃኛለን፡፡

ዛሬ ላይ አድናቆትን ያተረፉ ብዙዎቹ የስፖርት ኮከቦች ታሪካቸው የጀመረው በስታዲየም መብራቶች ስር ሳይሆን፣ በትምህርት ቤቶች አቧራማ ሜዳዎች ላይ ነው ማለት ይቻላል። ትምህርት ቤት ለአንድ አዳጊ የመጀመሪያው “የሙከራ ላብራቶሪ ነው፤ እዚያ ጋ ነው አሸናፊነት የሚቀመሰው፣ እዚያ ጋ ነው መውደቅና መነሳት የሚለመደው” የሚሉት ፕሮፌሰር ፓት ዴቪ ከአውሮፓ የስፖርት ማሰልጠኛ ምክር ቤት ጋር በመተባበር የስፖርት ተሰጥኦ ልማት መንገድ (Talent Development Pathway) በሚል ጥናት አካሂደዋል፡፡ በጥናታቸውም 80 በመቶ የሚሆኑት ስኬታማ ስፖርተኞች የመጀመሪያውን መነሳሳትና መሠረታዊ ክህሎት ያገኙት በትምህርት ቤት ውስጥ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ከትምህርት ቤት ተነስተው በስፖርቱ ዓለም ስኬት ካስመዘገቡ ስፖርተኞች መካከል ዓለም ስሙን በሁለት የስራ መስክ ጠንቅቆ የሚያውቀውን ጆርጅ ዌህን እናገኛለን፡፡ በስፖርቱ እና በፖለቲካው መስክ እውቅና ያገኘውና የዓለምን ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋች ክብር (Ballon d’Or) በማሸነፍ ብቸኛው አፍሪካዊ ጆርጅ ዌህ ሀገሩ ላይቤሪያን በፕሬዝዳንትነት አገልግሏል፡፡

ላይቤሪያዊው ስመጥር እግር ኳስ ተጫዋች መነሻው ትምህርት ቤት ስለመሆኑ እናገኛለን፡፡ ዌህ በሞንሮቪያ አዳጊ በነበረበት ወቅት፣ ትምህርት ቤቱ ለእሱ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን መጠለያውም ነበር። ትምህርት ቤት ባይኖር ኖሮ ተሰጥኦው የሚታይበት ሜዳም ሆነ የሚንከባከበው ስርዓት ባልተገኘ ነበር።

በትምህርት ቤት ውስጥ የሚደረጉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተራ ጨዋታዎች ሳይሆኑ፣ የታላላቅ ታሪኮች መጀመሪያ ስለመሆናቸውም ይረዳን ዘንድ የቅርጫት ኳሱ ንጉስ ሌብሮን ጀምስ ታሪክ ቀንጭበን እንመልከት፡፡ የእውቁ ስፖርተኛ ታሪክ የሚጀምረው በኦሃዮ ግዛት በሚገኘው ቅዱስ ቪንሰንት-ቅዱስ ሜሪ (St. Vincent-St. Mary) ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ሌብሮን በትምህርት ቤቱ ቡድን ውስጥ እያለ የሚያሳየው ብቃት እጅግ አስገራሚ ከመሆኑ የተነሳ፣ የትምህርት ቤቱ ጨዋታዎች በብሔራዊ ቴሌቪዥን በቀጥታ ይተላለፉ ነበር።

ትምህርት ቤቱ ለሌብሮን መሰረት ባይሆነውና ተሰጥኦውን የሚያሳድግበት ስርዓት ባይኖረው ኖሮ፣ ዛሬ የምናየውን ታላቅ ስፖርተኛ ላናገኝ እንችል ነበር። ሌብሮን ዛሬም ድረስ “ከትምህርት ቤት የወጣ ህፃን” (Just a kid from Akron) በሚል መሪ ቃል ትምህርት ቤቶችን ይረዳል፤ ምክንያቱም ለስኬቱ መነሻው ትምህርት ቤት እንደነበር ያውቃል ይላል የፎክስ ኒውስ ዘገባ።

የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ ኮከብና የአሁኑ የባረሰሎና እግር ኳስ ተጫዋች ራሽፎርድ ታሪክ ከትምህርት ቤት ጋር ጥልቅ ቁርኝት አለው። ራሽፎርድ በልጅነቱ በትምህርት ቤት በሚሰጥ ነፃ ምሳ እገዛ ማደጉን የቢቢስ ስፖርት ዘጋባ ያሳያል። የእግር ኳስ ተሰጥኦው ጎልቶ የወጣውም በትምህርት ቤቱ የእግር ኳስ ቡድን ውስጥ በነበረው ተሳትፎ እንደነበር የህይወት ታሪኩ ያስረዳል።

የዓለማችን ፈጣኑ ሰው ዩሴን ቦልት መጀመሪያ ላይ ፍላጎቱ እግር ኳስና ክሪኬት መጫወት ነበር። ነገር ግን ገና የመጀመሪ ደረጃ ተማሪ እያለ፣ የስፖርት መምህሩ የልጁን አስገራሚ ፍጥነት በማየት ወደ አትሌቲክስ እንዲዞር መከረው። ይህ የሚያሳየው በትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ መምህራን የተማሪን ተሰጥኦ በመለየትና አቅጣጫ በማሳየት ረገድ ያላቸውን የማይተካ ሚና ነው።

ወደ ሀገር ቤት መለስ ብለን የትምህርት ቤትና ስፖርት ግንኘነት ሲነሳ የአሁኑን ትውልድ በእጅጉ የሚያነሳሱ እንደነ ኃይሌ ገብረሥላሴ እና አትሌት ሰለሞን ባረጋ ያሉ አትሌቶችን እናገኛለን፡፡ ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ የሩጫ ህይወቱ አንድ ብሎ የጀመረው ወደ ትምህርት ቤት በሚያደርገው የየቀኑ የ10 ኪሎ ሜትር ጉዞ እንደነበር ይታወቃል።

ብዙዎች ሰለሞን ባረጋን የሚያውቁት በቶኪዮ ኦሎምፒክ የ10 ሺህ ሜትር ርቀትን በድል ሲያጠናቅቅና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ ሲያውለበልብ ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ ድል መነሻ የሆነው የቶኪዮው ታላቅ ስታዲየም ሳይሆን፣ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቱ በምትገኝ አነስተኛ የመጫወቻ ሜዳ እንደነበር የህይወት ታሪኩ ይነግረናል። እንደ ማንኛውም ተማሪ መማር ብቻ ሳይሆን፣ በትምህርት ቤቱ የስፖርት ክፍለ-ጊዜ እና በየዓመቱ በሚዘጋጁ የትምህርት ቤቶች ውድድር ላይ ተሳታፊ በመሆን ተሰጥኦውን መፈተሽ ጀመረ። በትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ የአካል ብቃት መምህራን ተሰጥኦን በመለየት ረገድ የነበራቸው ሚና ጉልህ ነው። መምህራኑ የሰለሞንን የጽናት ብቃት በማየት፣ “አንተ ትልቅ ቦታ ትደርሳለህ” የሚል ተስፋ በውስጡ መዝራታቸው ለዛሬው ስኬቱ እንደ ትልቅ ግብዓት ይጠቀሳል።

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረውና ለተከታታይ 15 ቀናት የሚቆየው 2ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች ስፖርት ሊግ እና የመምህራን ስፖርታዊ ውድድርም የተሰጥኦች መፍለቂያ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል። “በአካል ብቁና በአእምሮው ንቁ ትውልድ ለሀገር ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው 2ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች ስፖርት ሊግ እና የመምህራን ስፖርታዊ ውድድር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ነው የተጀመረው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፣ ትምህርትና ስፖርት ተመጋጋቢ መሆናቸውን በመጥቀስ ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው ውድድሩ የወጣቶችን ስፖርታዊ ክህሎት ከማሳደግ ባለፈ ጤናማና አምራች ዜጋን ለማፍራት ያለውን ፋይዳ ገልጸዋል።

የውድድሩ ዋነኛ ትኩረት ትምህርት ቤቶችን የተተኪ ስፖርተኞች መፍለቂያ ተቋማት ማድረግ መሆኑን የገለፁት አቶ በላይ፣ በቀጣይ 10 ዓመታት እንደ ሀገር አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን የመገንባት ግብ ለማሳካት ትምህርት ቤቶች ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል። መምህራን በውድድሩ መካተታቸውም በትምህርት ማህበረሰቡ መካከል ያለውን ማህበራዊ ትስስር እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቶች የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ከትምህርት ማህበረሰቡ በተጨማሪ ለአከባቢው ማህበረሰብ ክፍት እንደሚሆኑ ኃላፊው አሳውቀዋል። ለሁለት ሳምንት ገደማ በሚቆየው በዚህ ስፖርታዊ መድረክ እግር ኳስን ጨምሮ 12 የተለያዩ የስፖርት አይነቶች ለውድድር ቀርበዋል። ከ30 ሺህ በላይ  ስፖርተኞች ተሳታፊ ይሆናሉ።

ስፖርት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚከናወን ተራ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ሳይሆን፣ የተሟላ ስብዕና ያለው ዜጋ ለመቅረጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች ለስፖርት የሚሰጡት ትኩረት ሲጨምር፣ የሚገኘው በውጤቱ የሚመካ ተማሪን ብቻ ሳይሆን፤ በአካሉ ጤናማ፣ በስነ-ልቦናው ጠንካራና በቡድን የመስራት ጥበብ የዳበረ ትውልድን ነው።

በመሆኑም መምህራን፣ ወላጆችና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ስፖርትን ከትምህርት እኩል አውታር አድርገው ሊመለከቱት ይገባል። ዛሬ በትምህርት ቤት ሜዳ ላይ የምናፈሰው እያንዳንዱ ጠብታ ላብ፣ ነገ ለሚገኘው ስኬት ዋስትና በመሆኑ የነገዎቹን ሻምፒዮናዎች ለማፍራት ዛሬ በትምህርት ቤቶቻችን ሜዳ ላይ ዘር መዝራት የሁሉም የቤት ስራ ሊሆን ይገባል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review