AMN — ጥር 30/ 2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሎጎ ሀይቅ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ አካባቢው የሃይማኖቶች መከባበር ብቻ ሳይሆን የመዋረስና የሰላም ተምሳሌት መሆኑን ገልጸዋል።
ሀይቅ ከ10ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከተለያዩ ሀገራትና አቅጣጫዎች የመጡ ሰዎችን በሰላም ተቀብላ ያስተናገደች፣ ክርስትና እና እስልምና ተዋህደውና ተስማምተው በፍቅር የኖሩባት አስደማሚ አካባቢ መሆኗን ገልጸዋል።
ለአካባቢው ሕዝብ የሰላምና የትጋት ምስጢር ገዳሙ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ገዳሙ በዓላማው ሥራን፣ ትምህርትን እና ጾምን (ራስን መግዛትን) አስተባብሮ የያዘ በመሆኑ ለሀገር ታሪክ መጽናት ትልቅ ትምህርት እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

ይህ ፕሮጀክት ለትውልድ የሚጣል አሻራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሎጎ ሀይቅ ብልጽግናን ለሚጎናጸፈው ትውልድ እንደ መነሻ ነጥብ የሚታወስ የሀገር ታሪክ ማጽኛ ሀውልት መሆኑን ገልጸዋል።
ሎጎ ሀይቅ የመጣ ሰው ታሪክን ተምሮ፣ ፍቅርን ተጎንጭቶና የሰላም አየር ተንፍሶ የሚመለስበት ልዩ ስፍራ መሆኑን በመግለጽ፤ ይህ እሴት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ሊለመድ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳስበዋል።
በትዝታ መንግስቱ