AMN – የካቲት 2/2018 ዓ.ም.
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የቀድሞ ምክትል ኃላፊን ጨምሮ 11 አመራር እና ሠራተኞች በፖሊስ ተይዘው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
በፖሊስ ተይዘው ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች:-
አቶ ሞሊቶ አባይነህ ኤርቃሎ – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳዳር ቢሮ የቀድሞ ም/ኃላፊ
ኢ/ር ቸርነት አበበ የአደ – የቦሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት የቀድሞ ኃላፊ
ሰለሞን በላይ መኮንን – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳዳር ቢሮ የቴክኒክ ጉዳይ ወሳኝ ባለሙያ
አድማሱ አዳነ ወንድሙ – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳዳር ቢሮ የቅሬታ እና አቤቱታ ባለሙያ
ግዛቸው ሙሉጌታ ደሴ – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳዳር ቢሮ ይዞታ ማስተካከል ቡድን መሪ
ደረጀ ጎሹ ሀይሌ – የቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 13 የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ
አለምፀሃይ ለማ ኪ/ማርያም – የቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 13 መሬት ልማትና አስተዳደር የሰነድ አጣሪ ባለሙያ
ግርማ ተፈራ አያና – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳዳር ቢሮ ህግ/ቴክኒክ ጉዳይ ክትትል ዳይሬክተር
አማኑኤል አለማየሁ ማሞ – የቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 13 የቴክኒክ ባለሙያ
ቢኒያም ሀይሉ ገብሬ – የቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 13 የቴክኒክ ባለሙያ
አቢዮት ጁፋሬ ባይሳ – በአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ የወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር የነበሩ በቁጥጥር ስር ውለው በፍርድ ቤት ለተጨማሪ ምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆ ምርመራው ቀጥሏል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ እንደገለጸው ግለሰቦቹ ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በጥቅም ተመሳጥረው በሕዝብና በመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ያለአግባብ በመጠቀም ተጠርጥረዋል።
ክስ የተመሠረተባቸው በዋናነት በ2016 ዓ.ም. በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ቦታው አየር መንገድ አከባቢ የሕዝብ እና የመንግስት ይዞታ የሆነውን በ9ኛው መዋቅራዊ ፕላን በዓድዋ ፓርክነት ተይዞ የነበረውን እና በ10ኛ መዋቅራዊ ፕላን በዊንዶው ኦፍ አፍሪካ ልዩ ልዩ የከተማዉ መተንፈሻ አረንጓዴ ስፍራ ፕሮጀክት ሆኖ በከተማ ደረጃ በመናፈሻነት ለሕዝብ አገልግሎት የተያዘና በመሬት ባንክ ውስጥ ያለን ይዞታ “ሰነድ አልባ ይዞታ ነው” በማለት ለዮርዳኖስ፣ ዘውዲቱ እና ጓደኞቻቸው የሲሚንቶ አከፋፋይ ሕብረት ሽርክና ማኅበር እንዲተላለፍ አድርገዋል ተብለው ነው የተከሰሱት።
የቦታው የሊዝ ዋጋ 168 ሚሊየን 724 ሺህ 405 ብር የሚገመትን 2 ሺህ 905 ካ.ሜ ስፋት ያለውን መሬት ላይ ጉዳት በማድረስ ከወረዳ፣ ክ/ከተማ እና መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ድረስ በጥቅም ተሳስረዉ ስልጣንን ያለ አግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ናቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
ግለሰቦቹ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበው ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ምርመራው መቀጠሉን የአዲስ አበባ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ገልጿል።