ጥራት፣ ተመጣጣኝ ትርፍና የተረጋጋ ገበያ በአንድ ጥላ ስር የተገናኙበት የቅዳሜና እሁድ ገበያ በከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው

You are currently viewing ጥራት፣ ተመጣጣኝ ትርፍና የተረጋጋ ገበያ በአንድ ጥላ ስር የተገናኙበት የቅዳሜና እሁድ ገበያ በከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው

AMN- የካቲት 2/2018 ዓ.ም

ጥራት፣ ተመጣጣኝ ትርፍ እና የተረጋጋ ገበያ፤ እነዚህ ሶስት አውታሮች በአንድ ጥላ ስር የተገናኙበት የቅዳሜና እሁድ ገበያ በከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ሸማቾች ተናገሩ።

አምራቹን በቀጥታ ከሸማቹ ጋር በማገናኘት የዋጋ ንረትን ለመግታት እየተደረገ ያለው ጥረት፣ የንግድ ሰንሰለቱን በማሳጠር ረገድ ውጤታማ መሆኑን ነጋዴዎች እና ሸማቾች እየመሰከሩ ነው።

ኤ.ኤም.ኤን በመገናኛ እና በአያት 49 አካባቢ በሚገኙ የቅዳሜና እሁድ የገበያ ስፍራዎች ተገኝቶ ያነጋገራቸው ሸማቾች፣ ሸቀጥ አቅርቦት እና ጥራት መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወ/ሮ ኮኮቤ ስለሺ፣ ገበያው ጥሩ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ቃሪያ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና ድንች መግዛታቸውንነና ዋጋቸውም በጣም ተመጣጣኝ እንደሆነ አንስተዋል።

እንዲህ ያሉ አማራጮች በየቀበሌው እና በየአካባቢያችን ቢስፋፉ ዝቅተኛው ማህበረሰብ ኑሮውን ለማሻሻል ትልቅ ዕድል ይኖረዋል በማለትም ገልጸዋል።

ሌላኛዋ ሸማች ደግሞ ወይዘሮ እቴነሽ ወልደሃና ሲሆኑ፣ ጤፍ በኪሎ 110 ብር መግዛታቸውን እና ምርቱም ንጹህና ትኩስ መሆኑን ይናገራሉ።

እየቀረበ ያለው ሸቀጥ የተበላሸ ነገር እንደሌለበት በመግለፅም፣ እንዲህ ያለ አማራጭ መኖሩ ለአቅማችን ትልቅ ድጋፍ ነው ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ተንሳኤ ሳኅለማርየም በበኩላቸው፣ ነጭ ሽንኩርትና ሌሎች አትክልቶችን እንደገዙ በመናገር፣ የምርቶቹ ትኩስ መሆንና ዋጋውም ዝቅተኛ መሆኑ እንዳስደሰታቸው እና በዚህ መልኩ ቢቀጥል መልካም ነው ሲሉ ይናገራሉ።

በገበያ ቦታዎቹ ላይ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ ነጋዴዎችም፣ የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው የዋጋ ተመን መሠረት ለህብረተሰቡ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ እሱባለው አገልነህ የተባሉት ነጋዴ ድንችና ሽንኩርትን ጨምሮ ሌሎች ፍራፍሬዎችና አትክልቶችን ለገበያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ ነጋዴ ወ/ሮ በላይነሽ ቢሰጥ፣ እስከ አሁን ባለው ሂደት ገበያው በጣም ጥሩ መሆኑን በመግለጽ፣ ከደንበኞቻቸው ጋር በተረጋጋ ዋጋ እየተገበያዩ መሆኑን እና ያለምንም ቅሬታ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

አቶ በልስቲ አስረስ የተባሉት ነጋዴ በበኩላቸው፣ አቅርቦቱ በጣም ቆንጆ መሆኑን እና ዋጋው ቅናሽ በመሆኑ ህዝቡ በስፋት እየተጠቀመ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

እነርሱም የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው የዋጋ ተመን መሠረት ግብዓቶችን አሟልተው እያቀረቡ እንደሆነ እና በተመጣጣኝ ትርፍም እየሸጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ባለሙያዎችም በሥፍራው በመገኘት ገበያው እንዳይስተጓጎል ክትትል እና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ኤ ኤም ኤን መመልከት ችሏል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review