AMN – የካቲት 02/ 2018 ዓ.ም
የአፍሪካ ሀገራት በታሪካቸው ያጋጠሟቸውን ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ለመፍታት ሀገራዊ ምክክርን (National Dialogue/Peace and Reconciliation) እንደ ዋና መፍትሔ ተጠቅመውበታል።
ለአብነትም ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ቱኒዚያ እና ኬንያ ሀገራዊ ምክክር ካካሔዱ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህ ሀገራት ባካሄዷቸው ሀገራዊ የምክክር ሒደቶች ከተጠቀሟቸው መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
1. ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን
ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ምክክሩን የጀመሩት ከእርስ በርስ ጦርነት ወይም ከከፋ ግጭት በኋላ ነው። በዚህም የተነሳ ምክክሩ የነፍጥ ትግልን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት በመቀየር ደም መፋሰስ እንዲቆም ማድረግ ችሏል።
ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ስርዓት በኋላ ያደረገችው ምክክር ሀገሪቱ ወደ ከፋ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ከመግባት ታድጓታል።
2. አዲስ ሀገራዊ ትርክት መፍጠር
በመንግስትና በሕዝብ፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ብሔረሰቦች መካከል የነበረውን ጥርጣሬ በማስወገድ አዲስ የጋራ መመሪያ መቅረጽ አስችሏል፡፡
አሳታፊ የሆኑ አዲስ ሕገ-መንግስት እንዲረቀቅና የፖለቲካ ስልጣን ክፍፍል ፍትሐዊ እንዲሆን መንገድ ይከፍታል። ለምሳሌ ቱኒዚያ በሀገሪቱ ከተቀሰቀሰው “የጸደይ አብዮት” በኋላ በምክክር ሒደቱ አማካይነት ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድረግ ችላለች።

3. ብሔራዊ ዕርቅና ይቅርታ
ያለፈውን ታሪክ በማጤን፣ የተበደሉ ካሳ የሚያገኙበትና በዳዮች ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ የሚጠይቁበት መድረክ ይፈጥራል።
ቂምና በቀልን በመቀነስ ለወደፊት አብሮነት መሠረት ይጥላል። ሩዋንዳ ከዘር ማጥፋት እልቂት በኋላ የተጠቀመችበት የ”ጋቻቻ” ባህላዊ የምክክርና የፍርድ ሒደት ለሀገራዊ አንድነቷ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
4. የፖለቲካ ስርዓት ማሻሻያ
በምርጫ ወቅት የሚነሱ አለመግባባቶችንና የስልጣን ሽሚያዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ይረዳል።
ነጻ የሆኑ ተቋማት ማለትም ምርጫ ቦርድ እና ፍርድ ቤት እንዲገነቡ የጋራ አቅጣጫ ያስቀምጥላቸዋል። ለአብነት ያህል ኬንያ እ.ኤ.አ በ2007 ከነበረው የምርጫ ግጭት በኋላ ባደረገችው ምክክር ስር ነቀል የተቋማት ማሻሻያ አድርጋለች።
5. የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት መሠረት መጣል
ፖለቲካዊ መረጋጋት ባለበት ሀገር የውጭ ኢንቨስትመንትና የሀገር ውስጥ ልማት እንደሚጨምር ይታወቃል::
ስለዚህ በምክክር የምትጸና ሀገር በልማት አጀንዳዎች ላይ ብሔራዊ መግባባት መኖሩ መንግስት በተቀያየረ ቁጥር ፖሊሲዎች እንዳይቀያየሩና የሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ይረዳል።
ምንም እንኳን የሀገራዊ ምክክር ሒደቶች እንደየሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ውጤታቸው ቢለያይም፣ በዋናነት ግን የዕኔ ብቻ ሀሳብ ይደመጥ፣ ዕኔ ብቻ ልክ ነኝ፣ ዕኔ ብቻ ተበድያለሁ የሚለውን የከረረ አስተሳሰብ አስወግዶ በሌላው ጫማ ላይ በመቆም “ለጋራ ሀገር – የጋራ መፍትሔ” የሚለውን እሳቤ በእነዚህ ሀገራት በማስረጽ ትልቅ ውጤት አምጥቷል – ሀገራዊ ምክክር።
በአስማረ መኮንን