AMN- የካቲት 2/2018 ዓ.ም
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (DRC) ያላት እጅግ ግዙፍ የኮባልት ክምችት ለወደፊት ቴክኖሎጂዎች እና ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምርት ያለው ፋይዳ የመላው ዓለም ትኩረት ስቧል።
ይህንንም ተከትሎ በአሜሪካ፣ በቻይና እና በህንድ ባለሀብቶች መካከል የሚደረገው የሀብት ቁጥጥር ሽሚያ አዲስ ምዕራፍ መያዙ ተነግሯል።
በአሜሪካ የደኅንነትና የወታደራዊ ባለሙያዎች የሚመራው ቨርተስ ሚነራልስ ኢንክ፣ በኮንጎ የሚገኘውን ታዋቂ የማዕድን ኩባንያ የአፍሪካ ኬሚካሎች ለመግዛት ከስምምነት ላይ መድረሱ ታውቋል።
ኩባንያው የአፍሪካ ኬሚካሎች ቼፍን የኮባልት ሀብት ለመቆጣጠር በማለም፣ የኩባንያውን 900 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዕዳ ለመክፈልና ለፕሮጀክቶቹ ማስፋፊያ የሚሆን 750 ሚሊዮን ዶላር አዲስ ኢንቨስትመንት ለማፍሰስ ቃል ገብቷል።
የአፍሪካ ኬሚካሎች ቼፍ ምንም እንኳን ከፍተኛ የፋይናንስ ዕዳ ቢኖርበትም፣ በተለይ በሙቶሺ ፕሮጀክቱ ያለው እጅግ ሰፊ የኮባልትና የኮፐር ክምችት ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ተመራጭ አድርጎታል።
የአሜሪካው ቨርተስ ሚነራልስ ብቸኛው ተጫራች አይደለም በሂደቱ ላይ ቻይና እና ህንድ እየተሳትፉ ይገኛሉ፡፡
ቀደም ሲል የነበረው የሽያጭ ሙከራ በኮንጎ መንግሥት ተቀባይነት ባያገኝም፣ የቻይና ኩባንያዎች አሁንም በዘርፉ ያላቸውን የበላይነት ለማስጠበቅ እየጣሩ ነው።
እንደ ሊሎይድስ ሜታልና ኢነርጂ ያሉ የህንድ ኩባንያዎች ለአገራቸው የኢነርጂ ፍላጎት ዋስትና ለማግኘት በጨረታው ላይ እየተሳተፉ ነው።
በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው ጄካሚን የማዕድን ሀብቱ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች እጅ እንዲቆይ ወይም የተሻለ ድርሻ እንዲኖረው ጥረት እያደረገ ነው።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (DRC) በማዕድን ረገድ በዓለማችን እጅግ የበለፀገች ሀገር ተደርጋ ትቆጠራለች። የማዕድን ሀብቷ ግምት ከ24 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን ይገመታል። ሀገሪቷ የተለያዩ ውድ ማዕድናት ባለቤት ናት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ኮባልት፤መዳብ፤ታንታለም፤አልማዝ እና ወርቅ ተጠቃሽ ናችው፡፡
ኮንጎ በንጉሥ ሊዮፖልድ (ቤልጂየም) የግል ይዞታ በነበረችበት ወቅት፣ ለጎማ (Rubber) እና ለዝሆን ጥርስ ሲባል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተገድለዋል፣ እጅና እግራቸው ተቆርጧል። ይህም በታሪክ ውስጥ እጅግ አሰቃቂ ከሆኑ የሀብት ዘረፋዎች አንዱ ነው።
ኮንጎ ከዓለም እጅግ ባለጸጋ ሀገራት አንዷ ብትሆንም፣ ዜጎቿ ግን ከዓለም ደሃ ከሚባሉት ተርታ ትመደባለች፡፡ ይሁን እንጂ የማዕድን ሀብቱ ለሀገሪቱ ሰላም ከመንሳት ባለፈ ለጦርነት ነዳጅ ሆኗል፡፡
በታጣቂዎች መበራከት በተለይም በምስራቃዊ ኮንጎ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ወርቅ፣ ኮልታን እና ታንታለም የሚወጣባቸውን ቦታዎች በመቆጣጠር የጦር መሣሪያ ይገዙበታል። በዚህም ኮንጎያዊያን በማያባራ ጦረነት ውስጥ እንዲያልፉ ይገደዳሉ፡፡
የውጭ ጣልቃ ገብነትም ቢሆን ጎረቤት ሀገራትና አንዳንድ የውጭ ኃይሎች የማዕድን ዘረፋውን ለማቀላጠፍ ሲሉ አማጺ ቡድኖችን በመደገፍ ሀገሪቱ ሰላም እንዳታገኝ አድርጓታል።
ማዕድኑ ለሕዝቧ ብልጽግናን ከማምጣት ይልቅ መፈናቀልንና ሞትን አምጥቷል፡፡ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፤ ጅምላ ጭፍጨፋ እና መፈናቀል እና ከፍተኛ የሙስና እና የገንዘብ ዘረፋ አስከትሏል፡፡
ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ እንደዘገበው፣ ይህ ከፍተኛ የጨረታ ፉክክር የአፍሪካ የማዕድን ሀብት በተለይም የኮባልት ክምችት በዓለም አቀፍ የንግድና የጂኦ-ፖለቲካ መድረክ ላይ ያለውን የላቀ ጠቀሜታ በግልጽ የሚያሳይ ነው።
የኮንጎ የከርሰ-ምድር ሀብት የዓለም የኃይል ጉዞ አቅጣጫን የመወሰን አቅም እንዳለውም ዘገባው አመልክቷል።
በቶለሳ መብራቴ