የኢትዮጵያ አየር መንገድ በግማሽ ዓመቱ 4.4 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

You are currently viewing የኢትዮጵያ አየር መንገድ በግማሽ ዓመቱ 4.4 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

AMN- የካቲት 3/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በፈረንጆቹ 2025/26 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ 4.4 ቢሊየን ዶላር ገቢ በማግኘት፣ የዕቅዱን 102 በመቶ ማሳካቱን አስታውቋል።

አየር መንገዱ ይህንን የገለጸው የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ ነው።

የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ ባለፉት ስድስት ወራት ሦስት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎች ተጨምረዋል።

በዚህም አየር መንገዱ የሚበርባቸው የዓለም መዳረሻዎች ቁጥር 145 ደርሷል።

ከበረራ መዳረሻዎች ባሻገር፣ አየር መንገዱ የትራንስፖርት አቅሙን ለማሳደግ ግዙፉን A350-1000 አውሮፕላን ጨምሮ 7 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ገዝቶ ወደ ሥራ አስገብቷል።

ይህም አጠቃላይ የአየር መንገዱን የአውሮፕላን ቁጥር ወደ 147 አሳድጎታል።

በግማሽ ዓመቱ ውስጥ አየር መንገዱ የነበረው አፈጻጸም 10.6 ሚሊየን ደንበኞችን ያጓጓዘ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ11 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። 451 ሺህ ቶን ንብረት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች አጓጉዟል።

አየር መንገዱ የአገልግሎት ጥራቱንና ተደራሽነቱን ለማስፋት በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ መሆኑን አቶ መስፍን ጠቁመዋል።

በቅርቡ ግንባታው የተጀመረው የቢሾፍቱ (አዲስ) አየር ማረፊያ ዋነኛው ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም የሀገር ውስጥ በረራዎችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የ4 አየር ማረፊያዎች ግንባታ በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

በፍቃዱ መለሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review