አገልግሎቱ የፖሊስን አገልግሎት ዲጂታላይዝ የማድረግ እና ማኅበረሰቡ በነጻነት ወይም ምንም አይነት ጫና ሳይደርስበት በቀላሉ የሚፈልገውን መረጃ ለፖሊስ ማድረስ ያስችለዋል።
የወንጀል ጉዳይ፣ የተለያዩ አደጋዎች፣ የትራፊክ አደጋን ጨምሮ ማንኛውንም ጉዳይ በቀላሉ ለፖሊስ ማቅረብ የሚቻልበትን ስርዓት ነው።
አገልግሎቱ ምንም አይነት የሰው ንክኪ ሳይኖር ተገልጋዩ በቀላሉ አገልግሎቱን ማግኘት ያስችላል።
እስከዛሬ ስማርት ፖሊስ ጣቢያ አገልግሎት ላይ የዋለው በአውሮፓ እና እስያ ሶስት ሀገራት ሲሆን ዛሬ የተመረቀው በዓለማችን አራተኛው ስማርት ፖሊስ ጣቢያ በአፍሪካ ደግሞ የመጀመሪያው ያደርገዋል።
ስማርት ፖሊስ ጣቢያው በፖሊስ ሥራ ላይ ቀልጣፋነትን (efficiency) በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል።
ማንኛውም ባለጉዳይ ለፖሊስ ሪፖርት ካደረገ በኋላ ጉዳዩን ለመከታተል ያየው የነበረውን ውጣውረድ እና የማይመቹ ነገሮች ከሰው ጋር ያለውን ንክኪ እና ምልልስ በማስቀረት ጊዜና ጉልበት ይቆጥባል።
በቴክኖሎጂው አማካይነት አመራሩ በቀላሉ መረጃ ስለሚደርሰው ቶሎ ውሳኔ አስተላልፎ የሚፈለግ ወንጀለኛ፣ የጠፋ ነገር ወይም የደረሰ ጉዳት ካለ ፖሊስ ቶሎ ደርሶ ያንን ችግር በፍጥነት መፍታት የሚችልበትን ዕድል ይፈጥራል።
የወንጀል መከላከል እና የወንጀል ምርመራን ሥራን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።
ፖሊስ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ዕምነት እንዲያገኝ ያደርጋል።
የሕግ አስከባሪው አካል የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አካል በመሆን ለማኅበረሰቡ መረጃን በቀላሉ በራሱ ስልክ ወይም በስማርት ጣቢያዎች አማራጭ እንዲይቀርብ ዕድል ይፈጥርለታል።
ማኅበረሰቡ እያንዳንዱ ጉዳይ የፋይል ቁጥር ስለሚያገኝ በፋይል ቁጥሩ ጉዳዩን መከታተልና ፖሊስ ጣቢያ መሔድ ሳይጠበቅበት ተጨማሪ መረጃ ካለበት ቦታ ሆኖ መላክና እስከፍርድ ቤት ድረስ ጉዳዩን መከታተል ይችላል።
በተለይ ግለሰቦች የተለየ መረጃ ይዘው ወይም ጉዳያቸውን ለኃላፊ መናገር ሲፈልጉ በቀላሉ እዚህ መጥተው ኃላፊውን በቀጥታ (live) እያገኙ በቀላሉ ጉዳያቸውን ማስረዳት የሚችሉበትን ዕድል ጭምር የፈጠረ ትልቅ ብሥራት ነው።
በሚካኤል ኅሩይ