AMN – የካቲት 3/2018 ዓ.ም
በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በሚያደርግ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ለመቀበልና ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸዉን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
አዲስ አበባ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች አምራና ተዉባ 39ኛውን የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ላይ ታስተናዳለች፡፡ የጉባዔዉ ተሳታፊዎችም ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል፡፡
ጉበዔዉ የተገነቡት የልማት ስራዎች በአፍሪካና በአለም ደረጃ የሚተዋወቁበት ብቻ ሳይሆን የነዋሪው እንግዳ ተቀባይነት በተግባር የሚመሰክርበት ልዩ መድረክ መሆኑን የመዲናዋ ነዋሪዎች ለኤኤምኤን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ደነቀው አብረሃም እንደሚሉት፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት እንግዶች ሲመጡ ከአውሮፕላን ማረፊያ ወደ ሆቴልና ወደ ስብሰባ አዳራሽ ብቻ ነበር የሚወሰዱት።
አሁን ግን ከተማዋ እንግዶችን ልታስጎበኝ የምትችልባቸው እንደ የአድዋ ድል መታሰቢያ፣ አራዳና እንጦጦ ፓርኮች፣ የሳይንስ ሙዚየም እና የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ያሉ በመንግሥትና በሕዝብ ተሳትፎ የተገነቡ የልማት ውጤቶች ባለቤት ሆናለች።
የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ደረጀ ጌታቸውና ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር እንደገለጹት፣ ፖሊስና ነዋሪው ተቀናጅተው ለደህንነት ስራው ሌት ተቀን እየሰሩ ይገኛሉ። እንግዳ ተቀባይነቱ በንግግር ብቻ ሳይሆን በመተሳሰብ፣ በመከባበርና ያለንን ትዉፊት በማሳወቅ በተግባር መገለጥ አለበት፡፡
የ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ አዲስ አበባን እንደ አፍሪካ መዲናነቷ ብቻ ሳይሆን፣ የለውጥና የልማት ተምሳሌት አድርጎ ለማሳየት ትልቅ ዕድል መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎች እንግዶች ያለምንም የዋጋ ጭማሪና እንግልት የከተማዋን ውበት እንዲያዩ እና እንዲሸምቱ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ