AMN የካቲት 03 ቀን 2018 ዓ.ም
በ26ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መርሐግብር ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይከናወናሉ፡፡ በማይክል ካሪክ እየተመራ ተከታታይ ድል እያስመዘገበ የሚገኘው ማንችስተር ዩናይትድ ወደ ለንደን አቅንቶ ዌስትሃም ዩናይትድን ይገጥማል፡፡
ማይክል ካሪክ በተጫዋችነት ዘመኑ ከዌስትሃም ዩናይትድ ጋር ያለው ቁርኝት ትልቅ ነው፡፡ እንግሊዛዊው የቀድሞ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች በቶተንሃም እና በማንችስተር ዩናይትድ ምን መስራት እንደሚችል ከማሳየቱ በፊት በዌስትሃም ነው ተኮትኩቶ ያደገው፡፡ በዌስትሃም አካዳሚ አድጎ ለዋናው ቡድን 136 ጨዋታዎችን ካከናወነ በኋላ ነበር 2004 ላይ ለቶተንሃም የፈረመው፡፡
ማይክል ካሪክ ዩናይትድን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ከተረከበ በኋላ ውጤታማ ጉዞውን ለማስቀጠል ወደ አደገበት የደቡብ ለንደኑ ክለብ ያቀናል፡፡ ዩናይትድ ማንችስተር ሲቲ ፣ አርሰናል ፣ ፉልሃም እና ቶተንሃምን በማሸነፍ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሚያሳትፈው ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በዛሬው ጨዋታ በማንችስተር ዩናይትድ በኩል ሜሰን ማውንት እና ማቲያስ ደሊግት ወደ ልምምድ ቢመለሱም አይሳተፉም፡፡ ዌስትሃም ዩናይትድ ቅጣት ላይ የሚገኘው ዦን ክሌር ቶዲቦን አያሰልፍም፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ ምንም እንኳን ጥሩ ብቃት ላይ ቢገኝም ከዌስትሃም ዩናይትድ ጋር ያለው የቅርብ ጊዜ ግንኙነት በውጤት የታጀበ አይደለም፡፡ ዌስትሃም ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር በሜዳው ባደረጋቸው ሦስት የመጨረሻ ጨዋታዎችን አሸንፏል፡፡
ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኘው ዌስትሃም ይህን የበላይነቱን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ ማንችስተር ዩናይትድ በአንፃሩ አምስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማግኘት ይፋለማል፡፡
በለንደን ኢሊምፒክ ስታዲየም ሚከናወነው ጨዋታ ምሽት 5፡15 ላይ ይጀምራል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች በሊያም ሮሲኒኦር እየተመራ አራት ተከታታይ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ያሸነፈው ቼልሲ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ ሊድስ ዩናይትድን ያስተናግዳል፡፡
ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከኒውካስትል ዩናይትድ እንዲሁም ኤቨርተን ከቦርንማውዝ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም ይጠበቃሉ፡፡ ሦስቱም ጨዋታዎች ምሽት 4፡30 ላይ ይጀምራሉ፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ