AMN — የካቲት 03/2018 ዓ.ም
ብልፅግና ቀጣይነት ያለው በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት ማስፋፋት ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫው መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር! የብልፅግና ፓርቲ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ይፋ ማድረጊያ መድረክ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በመድረኩም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ፣ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፣ የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት እና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አመራር አባላት ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር! የብልፅግና ፓርቲ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በመሪ መልዕክትነት ተሰይሟል።
የብልፅግና ፓርቲ የዘንድሮው ጠቅላላ የምርጫ ምልክት የስንዴ ነዶ የመደመር፣ የአንድነትና የትብብር ተምሳሌትነትን የሚወክልና የምርታማነት መገለጫ መሆኑም ተገልጿል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ብልፅግና ከትላንት የሚወሰዱ እሴቶችን በመገንዘብ፣ የሚወረሱትን አምዶች አውቋል።

ከነዚህም በመነሳት አዋጭ የሆነውን የኢትዮጵያ ጉዞ መተለሙን ጠቁመው፤ የብልፅግና የምርጫ ማኒፌስቶ የያዘውም ይህንኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ብልፅግና ለዲጂታላይዜሽን በሰጠው ልዩ ትኩረት እና ባከናወናቸው ስራዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።
የዲጂታል ፋይናንሲንግ አካታችነትን ከማረጋገጥ አኳያ ፓርቲው በተጨባጭ ሰፊ ርብርብ ማድረጉን ገልጸዋል።
ብልፅግና ቀጣይነት ያለው በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት ማስፋፋት ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫው መሆኑንም ተናግረዋል።
አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ከማድረግ ባለፈ እርስ በእርሳቸው ማስተሳሰር ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል መስጠት መጀመሩን አንስተዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በፌዴራል ደረጃ ተግባራዊ በማድረግ፣ አሁን ላይ አገልግሎቱን ወደ ክልል እና ከተማ አስተዳደሮች መስፋፋቱንም ጠቁመዋል።
መሶብ በተጀመረባቸው አካባቢዎችን የተገልጋዮች እርካታ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ዋነኛው ምሰሶ የሰው ሀብት ልማት መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠናን ተግባራዊ ማድረጉንም ተናግረዋል።
ብልፅግናን መምረጥ በዲጂታል ኢትዮጵያ ነጋችንን ብሩህ ማድረግ መሆኑን አመልክተው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ኢኒሼቲቮች የተገኙ ውጤቶች ኢትዮጵያውያን ቀና ማለት እንደሚችሉ ያሳዩበት መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።