AMN የካቲት 3/2018
ብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያን የተጽዕኖ አድማስ ለማስፋትና የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሠራ በምርጫ ማኒፊስቶው ማረጋገጡን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን ፓርቲው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወከልበት የምርጫ ምልክቱ የስንዴ ነዶ መሆኑን አስታውቋል።
አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት፤ ፓርቲው በ”መደመር” እሳቤ በመመራት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለዘመናት የቆዩ መዋቅራዊ ስብራቶችን በመጠገን፣ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል።
ፓርቲው ህዝብን በማሳተፍ፣ በጽናትና ቁርጠኝነት ስኬቶችን ሲያረጋግጥ መቆየቱን ጠቅሰው፤ የህዝብ ይሁንታ በማግኘት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውጤታማ ጉዞ ማስቀጠል የሚያስችለውን የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ማኒፊስቶ አዘጋጅቶ ይፋ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

ማኒፌስቶው ብልፅግና ፓርቲ በመደመር እሳቤ በመመራት እስካሁን ያስመዘገባቸውን ስኬቶች፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችንና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በዝርዝር የያዘ መሆንን አብራርተዋል።
ማኒፌስቷችን ትናንትን ማከምን፣ ዛሬን በአግባቡ መጠቀምንና ነገን መተንበይን ማዕከል ያደረገ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
በማኒፌስቶው ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የዲፕሎማሲው ዘርፍ ቀዳሚውን ስፍራ መያዙን ጠቁመው፤ ፓርቲው በቀጣይ አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን የተጽዕኖ አድማስ ለማስፋትና የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰራ በማኒፌስቶው ይፋ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ከጎረቤትና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት፣ ከብሪክስ አባል ሀገራትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራም በማኒፌስቶው መገለጹን አስታውቀዋል፡፡
እንዲሁም በዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ ውስጥ የሚዛናዊነት መርህን በመከተል የኢትዮጵያን ተደማጭነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተካትቷል ብለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ በማኒፌስቶው ይፋ እንዳደረገው፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር የሚያጠናክሩ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን ተግባራዊ ማድረግና የዜጎችን ክብር ማስጠበቅ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡
አባይን በፍትሃዊነት የመጠቀምና አስተማማኝ የባህር በር የማግኘት መብታችንን ለማስከበር የጀመርናቸውን ጥረቶች እንደምናሰፋ በማኒፌስቶው በግልጽ ተቀምጧል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ለዚህም ሰላማዊ፣ ህጋዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረጉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በማኒፌስቶው ማካተቱን አረጋግጠዋል።