ያልወረደ የዘር ፍሬ በወንድ ህፃናት ላይ የሚያስከትለው አደጋና መፍትሄው

You are currently viewing ያልወረደ የዘር ፍሬ በወንድ ህፃናት ላይ የሚያስከትለው አደጋና መፍትሄው
  • Post category:ጤና

AMN – የካቲት 4/2018 ዓ.ም

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህፃናት ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ውብእድል ክፍሉ፣ በወንድ ህፃናት ላይ ስለሚታየውና አስቸኳይ ትኩረት ስለሚሻው ያልወረደ የዘር ፍሬ (Undescended Testicle) የጤና እክል ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ (AMN) ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የወንድ የዘር ፍሬ መጀመሪያ የሚፈጠረው በህፃኑ ሆድ ውስጥ ሲሆን፣ ህፃኑ ሳይወለድ በፊት ቀስ በቀስ ከሆድ በመውጣት ወደ ከረጢቱ (Scrotum) ይወርዳል።

ሆኖም በአንዳንድ ህፃናት ላይ ፍሬዋ በከረጢቱ ውስጥ ሳትቀመጥ መንገድ ላይ (ብሽሽት አካባቢ) ወይም ሆድ ውስጥ ልትቀር ትችላለች።

ይህ ችግር በወቅቱ ካልታከመ ለከፋ የጤና እክል አልፎም ለካንሰርና ለመሃንነት ሊዳርግ እንደሚችል ዶክተሯ ያስጠነቅቃሉ።

ለምን አስቸኳይ ትኩረት ያስፈልገዋል?

የዘር ፍሬ በተፈጥሮዋ ከሰውነት ሙቀት በታች በሆነ ቀዝቃዛ ቦታ (ከረጢት ውስጥ) መሆን አለባት።

ፍሬዋ ሆድ ውስጥ ወይም ብሽሽት አካባቢ ስትቆይ ግን ለከፍተኛ ሙቀት ትጋለጣለች። ይህም የሚከተሉትን አደጋዎች ያስከትላል፦

• የካንሰር ተጋላጭነት፦ ለሞቃት አካባቢ የተጋለጡ የዘር ፍሬ ሴሎች መደበኛ ያልሆነ እድገት በማሳየት ወደ ካንሰር የመቀየር እድላቸው ከፍተኛ ነው።

• የመጠምጠም አደጋ (Torsion)፦ ፍሬዋ በብሽሽት አካባቢ ስትሆን የመሽከርከርና እራሷ ላይ የመጠምጠም አደጋ ያጋጥማታል። ይህም የደም ዝውውር በማቋረጥ ፍሬዋ እንድትሞት ሊያደርግ ይችላል።

• የመሃንነት ስጋት፦ በተለይ ሁለቱም የዘር ፍሬዎች ካልወረዱ፣ የዘር ፍሬ የማምረት አቅም ስለሚቀንስ ለወደፊት ልጅ የመውለድ እድልን በእጅጉ ያጠባል።

ያለጊዜያቸው በተወለዱ ህፃናት ላይ ፍሬዋ እስከ ስድስት ወር ድረስ ላትወርድ ትችላለች የሚሉት ዶክተር ውብእድል፣ ከስድስት ወር በኋላ ግን በራሷ ትወርዳለች ተብሎ እንደማይጠበቅ ይገልጻሉ።

ችግሩ ላጋጠማቸው ህጻናት ቀዶ ጥገና መሰራት ያለበት ከሆነ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወር (በአማካኝ አንድ ዓመት ላይ) ሊሰራ ይገባል።

እንደ ቀድሞው እስከ አምስት ወይም ሰባት ዓመት መጠበቅ በሳይንሳዊ ምርምር ተቀባይነት የለውም፤ አደጋዎቹን ለመከላከል ህክምናው ቀድሞ መደረግ አለበት።

የወላጆች ድርሻ ምንድነው?

ቤተሰቦች የልጆቻቸውን አካል በትኩረት በመመልከት የሚከተሉትን ነጥቦች ማረጋገጥ እንዳለባቸው ዶክተሯ ይመክራሉ፦

• የከረጢቱን ቅርጽ ማየት፦ ፍሬው የወረደለት ህፃን ከረጢቱ ሞላ ብሎ ይታያል፤ ያልወረደለት ግን የሰለለ ወይም የተሸበሸበ ይሆናል።

• በመዳሰስ ማረጋገጥ፦ ህፃኑን ገላ ሲያጥቡ ወይም ልብስ ሲቀይሩ በከረጢቱ ውስጥ ድድር ያለች ፍሬ መኖሯን በእጅ ዳስሶ ማረጋገጥ ይቻላል።

• መደበኛ ምርመራ፦ በዓመት አንድ ጊዜ የህፃናት ሐኪም (Pediatrician) ዘንድ በመውሰድ አጠቃላይ የጤና ምርመራ (Check-up) ማድረግ ችግሩን ቀድሞ ለማወቅ ይረዳል።

በልጅዎ ላይ ማንኛውም አይነት ልዩነት ካዩ ሳይዘገዩ ወደ ጤና ባለሙያ በመሄድ ምክርና ህክምና ያግኙ።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review