ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ስብራቶችን ጠግኖ ብርሃናማ የወደፊት ተስፋን የሚሰንቅ የእውነት ፍለጋ ሂደት ነው – ዮናስ አዳየ (ዶ/ር)

You are currently viewing ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ስብራቶችን ጠግኖ ብርሃናማ የወደፊት ተስፋን የሚሰንቅ የእውነት ፍለጋ ሂደት ነው – ዮናስ አዳየ (ዶ/ር)
  • Post category:ፖለቲካ

AMN — የካቲት 04/ 2018 ዓ.ም

ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ስብራቶችን ጠግኖ ብርሃናማ የወደፊት ተስፋን የሚሰንቅ የእውነት ፍለጋ ሂደት መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳየ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ምክክር በዘመናት ሂደት በትርክት፣ በታሪክና በማንነት ሰበብ የተቀበሩ ቅራኔዎችን እውነቱ የቱ ጋ ነው? ብሎ በንግግር የማግኘት ሂደት መሆኑንና ሰዎች አንዱ በሌላው ቦታ ሆኖ ችግሮችን ለመፍታት የሚተያዩበት፣ የሚከባበሩበትና ካለፈው ስህተት ተምረው አዲስ ህይወት የሚገነቡበት መድረክ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለው የመኖር ውል ሲላላና የታጠቁ ኃይሎች በየቦታው ህዝቡን ሲያማርሩ ምክክር የግድ ያስፈልጋል ያሉት ዮናስ አዳየ (ዶ/ር) ባለፉት አርባ እና ሀምሳ ዓመታት የተፈጠሩ መጤ ጽንፈኛና ጠባብ አመለካከቶች ያመጡትን የዘረኝነትና የመንደርተኝነት ስብራት ለመጠገን ብቸኛው መንገድ ሀገራዊ ምክክር ነው ብለዋል።

የሀገራዊ ምክክር አላማዎች በቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ፣ በመንግስትና በህዝብ እንዲሁም በህዝብና በህዝብ መካከል የጠፋውን እምነት መመለስ እና ቅሬታ ሲኖር ወደ ጫካ ከመግባት ይልቅ ውይይትንና ምክክርን ባህል ማድረግ እንደሆነም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡

የእኔ የማትሆን ኢትዮጵያ ትጥፋ የሚለው አደገኛ አመለካከት የፖለቲካ ስብራት ውጤት መሆኑን የጠቀሱት ዮናስ (ዶ/ር)፤ ኮሚሽኑ በቡድንና በብሄር ከመታጠር ይልቅ እውነትን መሰረት ያደረገ የጋራ ሀገርና የጋራ ትርክት እንዲኖር የፈውስ ሚና እንደሚጫወት አስታውቀዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የምክክር ሂደቱ የተሳካለቸው ሀገራት መነሻ አድርገው የተነሱት የራሳቸውን ችግር በራሳቸው በመመካከርና በመነጋገር የቻሉት ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ሳይሳካላቸው የቀሩት ደግሞ ሌሎች ሀገራት ጣልቃ በመግባት ሂደቱን የመሩት መሆናቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለአብነትም የየመን የምክክር ሂደት በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በመጠለፉ ምክንያት ሳይሳካ ሲቀር፤ የቱኒዚያ ግን በሀገር በቀል ጥረት በመከናወኑ ውጤታማ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ሂደት በኢትዮጵያውያን፣ ለኢትዮጵያውያን የሚከናወን በመሆኑ ስኬቱ እጅግ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ሲሳካ ኢትዮጵያን በፖለቲካና በኢኮኖሚ ሀያልና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንደሚያደርጋትም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳየ (ዶ/ር) ከኤኤምኤን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ገልጸዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review