የመንገድ ዳርና የውስጥ ለውስጥ መብራቶች መሟላት በጨለማ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመቀነስና የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ ቁልፍ ሚና እንዳለው ተገለፀ

You are currently viewing የመንገድ ዳርና የውስጥ ለውስጥ መብራቶች መሟላት በጨለማ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመቀነስና የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ ቁልፍ ሚና እንዳለው ተገለፀ

AMN- የካቲት 4/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በመገኘት ከዚህ ቀደም በምሽት ለመንቀሳቀስ ስጋት የሆኑ እና ወንጀል የሚከሰትባቸዉ ቦታዎች አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ብርሃናማ የሆኑ ስፍራዎችን ተዘዋውሮ የመስክ ምልከታ በማድረግ አፈፃፀሙን ገምግሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ በመስክ ምልከታ ወቅት እንደገለጹት፤ የመብራት ማስበራት መርሃ ግብሩ ጨለማን በብርሃን በመተካት የወንጀል ስጋቶችን ለመቀነስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ከተማዋ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑባት እንደመሆኗ መጠን፣ አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን አንዱ ክፍለ ከተማ ከሌላው ተሞክሮ በመውሰድ የጋራ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባው አሳስበዋል።

በተጨማሪም ከተማዋን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የደህንነት ስርዓት እንዲኖራት ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኃላፊዋ ገልጸዋል። ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ እና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት ለወንጀል መንስኤ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት፣ ሊከሰቱ የሚችሉ ወንጀሎችን የመከላከልና የመቀነስ ስራ በስፋት መከናወኑን አስረድተዋል።

ይህም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተጠናከሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል ።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና እንደገለጹት፤ በክፍለ ከተማው “ሞዴል ብሎኮችን” በመፍጠር ረገድ ውጤታማ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል። ባለፉት ጊዜያት ከተማዋ በልማት ረገድ ትልቅ ለውጥ ማሳየቷን ጠቅሰው፣ የክፍለ ከተማው የፀጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በቅንጅት በመስራታቸው በርካታ ብሎኮችና ቀጠናዎችን ከስጋት ነፃ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

የፀጥታ አጠባበቁን ይበልጥ ለማዘመንና ዘላቂ ለማድረግ አንዳንድ ብሎኮች በክትትል ካሜራ እንዲደራጁ እየተደረገ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል። ይህ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፀጥታ አጠባበቅ ስራ በእቅድ ተይዞ እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን፣ በቀጣይም የህዝቡን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በመሀመድኑር ዓሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review