AMN- የካቲት 4/2018 ዓ.ም
48ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ለጉባኤው ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚህ ጉባኤ የሰላም፣ የጸጥታ፣ የአየር ንብረት እና የውሃ ሀብት ጉዳዮች ላይ ተጨባጭ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ባለፉት አመታት አፍሪካ ዘርፈብዙ የልማት ስኬቶችን ብታስመዘግብም አጀንዳ 2063’ን ለማሳካት ከተቀመጡት ግቦች አንፃር ገና ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚያስፈልግ ጊዲዎን (ዶ/ር) አብራርተዋል።
የዘንድሮው የህብረቱ ጉባኤ ውሃ ሀብት ላይ አተኩሮ የሚካሄድ እንደመሆኑ፤ በዘርፉ ሊተኮርባቸው ይገባል ያሏቸውን ነጥቦችም አንስተዋል። የበርካታ ግዙፍና ረዣዥም ወንዞች ባለቤት የሆነችው አፍሪካ የውሃ ሀብቷን በአግባቡ በመጠቀም ቀጣይነት ላለው ልማት ማዋል እንደሚገባትም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና የአባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጉባዔው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ይታያል አጥናፉ