የካቲት 4/2018 ዓ.ም
በአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ነፃነትን ለማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ ውህደትን እና የጋራ ብልጽግናን ለማሳካት ወሳኝ መድረክ ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።
የአፍሪካ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በማራመድ ረገድ ህብረቱ እያደገ ያለውን አስተዋፅኦ አጉልተው ገልጸዋል። ይህም የተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤት ማሻሻያዎችን ለማድረግ ፣ የአየር ንብረት ፍትህ ለማስፈን እና የዓለም የፋይናንስ ስርዓቱን መልሶ ማዋቀርን በተመለከተም ወሰኝ ስራ እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል።
በአህጉሪቱ በርካታ አዎንታዊ ለውጦችን እንዳሉ የገለፁት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከእነዚህም ውስጥ በርካታ አገሮች የተሳካ ምርጫ አካሂደዋል፣ የተወሰኑ ሀገራት ወደ ኅብረት አባልነት መመለስን ጨምሮ በተጨማሪም የአባል አገራት በአፍሪካ ህብረት የምርጫ ክትትል እና የድጋፍ ተልዕኮዎች ላይ ያላቸው እምነት እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል።
ከዚህ በተቃራኒም አፍሪካ በርካታ ፈተናዎችን መጋፈጧን አንስተዋል። በተለይም ሕገ መንግሥታዊ ያልሆኑ የመንግስት ለውጦች እና ሰላምን እና ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ዓለም አቀፍ የጂኦፖሊቲካል ተለዋዋጭ ለውጦችን እያስተናገደች እንደምትገኝ ዶ/ር ጌድዮን አብራርተዋል።
አፍሪካ የውጭ የበላይነትን ውድቅ ማድረግ እና በምትኩ በእኩልነት እና በጋራ መከባበር ላይ የተገነቡ እውነተኛ አጋርነቶችን መከተል እንዳለባት አፅንዖት ሰጥተዋል።
በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ላይ ያላሳለሰጥረት በማድረግ አፍሪካ በአጀንዳ 2063 እና በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) በኩል ቀጣናዊ ውህደት ጉልህ እመርታ እንዳሳየችም ዶ/ር ጌድዮን ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ለቀጣይ አጋርነታቸው በማጠናከር በዚህ ውይይትም የአህጉሪቱን ጥቅም የሚያሳድጉ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ይታያል አጥናፉ