AMN- የካቲት 5/2018 ዓ.ም
መንግስት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት፣ ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ካለበት 30 በመቶ ወደ 45 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገልጸዋል።
ምክትል ከንቲባው ይህንን የገለጹት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ለዘርፉ ውጤታማነት እውቅና ለመስጠት በተዘጋጀ መድረክ ላይ ነው።
ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የነበሩ ማነቆዎችን በመፍታት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉንም አቶ ጃንጥራር አመልክተዋል።
የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት (GDP) የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከ30 በመቶ ወደ 45 በመቶ አድጓል፡፡
ለአምራቾች ምቹ የገበያ ትስስር በመፈጠሩ ምርታማነት እንዲጨምር ሆኗል።
የውጭ ምንዛሬን ለማዳን የሚያስችሉ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ስራ ውጤት እያሳየ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ምክትል ከንቲባው አክለውም፣ አሁን የተመዘገበውን ውጤት ይበልጥ ለማሳደግ የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ፣ አመራሮች ለአምራች ዘርፉ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
በተያያዘም የኮልፌ ክፍለ ከተማ የኢንዱስትሪ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ የኔው ሞሴ፣ መንግስት ለአምራቾች የሰጠው ትኩረት ትልቅ አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል።
በመሆኑም በስራቸው የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች ቢሮው እውቅና መስጠቱን ተናግረዋል።
በአልማዝ ሙሉጌታ