AMN- የካቲት 7/2018 ዓ.ም
አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ የሚገባትን ውክልና እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንድታገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጥሪ አቅርበዋል።
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አህጉሪቱ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን፣ ይህ 2026 እንጂ 1946 አይደለም ሲሉ አስምረውበታል።
ዋና ጸሐፊው በሱዳን፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በሶማሊያ እና በሌሎች የአህጉሪቱ ክፍሎች ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይም የአፍሪካ የሰላም ድጋፍ ተግባራት አስተማማኝ ፋይናንስ እንዲያገኙ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
አፍሪካ ለዓለም የአየር ንብረት መዛባት የምታበረክተው አስተዋጽኦ አነስተኛ ቢሆንም፣ የችግሩ ግን ቀዳሚ ተጠቂ መሆኗን ጉተሬዝ አስታውሰዋል።
አህጉሪቱ ካላት የፀሐይ ኃይል አቅም ውስጥ የምታገኘው ኢንቨስትመንት 2 በመቶ ብቻ መሆኑ አግባብ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ “ምዝበራ ይቁም፤ የአፍሪካ ሀብት ለአፍሪካ ሕዝብ ይሁን” ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።
ዋና ጸሐፊው አያይዘውም የሥራ ዘመናቸው እስከሚያበቃበት ጊዜ ድረስ ከአፍሪካ ጎን እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።
በታምራት ቢሻው