የአፍሪካ ከተሞችን ገፅታ በመቀየር ምቹ ሁኔታን መፍጠር ይገባል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የአፍሪካ ከተሞችን ገፅታ በመቀየር ምቹ ሁኔታን መፍጠር ይገባል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- የካቲት 7/2018 ዓ.ም

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመክፈቻ ስነ-ስርአቱ ባደረጉት ንግግር፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የከተማና የገጠር ከተሞችን ይበልጥ ምቹ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀና ለሰው ልጅ የሚስማሙ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህም ማሳያ የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት በምሳሌነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ባከናወናቸው ተግባራት የቆሸሹ ወንዞችን በማልማት ወደ ንፁህና የህዝብ መዝናኛ ስፍራነት መቀየራቸውን አንስተዋል።

የመዲናዋ የወንዝ ዳርቻ ልማት የጎርፍ አደጋ ስጋትን ከመቀነሱም ባሻገር፣ ተጨማሪ ውበትና ክብርን ያጎናፅፋል ብለዋል።

የአፍሪካ የከተሞች ገፅታን በፍጥነት በመለወጥ፣ የወደፊቷ አፍሪካ ከተሞች ለእግረኛ ምቹ፣ አረንጓዴ፣ በወጣቶች ላይ ያተኮረችና የተመሰረተች መሆን አለባት ብለዋል ።

የአካባቢ ስነ-ምህዳርን በማደስና ለቀጣዩ ትውልድ ህያው ቅርስ ለማስቀመጥ በማለም በ”አረንጓዴ አሻራ” ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል መቻሉን አንስተዋል።

ለአየር ንብረት ብክለት ድርሻ የሌላት አፍሪካ፣ ብክለቱ ጫና ማሳደሩን ገልፀዋል።

በመሆኑም የአየር ንብረት እርምጃዎች በፍትሃዊነት ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው ሲሉም አንስተዋል።

ስለሆነም በፋይናንስና ቴክኖሎጂን በማቀናጀት አፍሪካ ሁለንተናዊ ዕድገት እንድታስመዘግብ ማስቻል እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review