AMN የካቲት 7/2018
የአፍሪካን ዘላቂ ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐመድ አሊ የሱፍ ገለጹ።
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፥ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐመድ አሊ ዩሱፍ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐመድ አሊ የሱፍ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የጉባኤው መሪ ሀሳብ በሆነው ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ለኢኮኖሚያችን ቁልፍ ነው፤ ለሰላምና ትብብርም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
አፍሪካን ከውጭ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል አህጉራዊ አንድነትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተናግርዋል።
የፋይናንስ ተቋማት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን እና የአፍሪካ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ በአንድነት መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የፓን-አፍሪካ ተቋማት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ ኒፓድ እና የአፍሪካ ሲዲሲ ጥረታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።
አህጉሪቱን ለመደገፍ የሀገር ውስጥ ሀብትን ማሰባሰብ ምርጫ ሳይሆን አስገዳጅ ተግባር ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ዕቅዶች የወጣቶችን እና የሴቶችን የእኩልነት ጥያቄ መመለስ አለባቸው ብለዋል።
የግብርናውን ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪያዊ የግብርና ማቀነባበሪያ ማሸጋገር፣ የመሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት የኢነርጂና ኢንዱስትሪ ልማትን ማፋጠን ይገባል ብለዋል።