AMN የካቲት 07 ቀን 2018 ዓ.ም
በዓለም-ዓቀፉ እግርኳስ ፌዴሬሽን (FIFA) በአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) እንዲሁም በ World Athletics ባስቀመጡት ደረጃ መሰረት በአዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው የአቃቂ ኢንተርናሽናል ስቴዲየም የመጫወቻ ሜዳ ቅልቅል (Hybrid turf) ሳር ንጣፍ ስራ ተጀምሯል፡፡
በአውሮፓ እና በአፍሪካ በሚገኙ ትልልቅ ስታዲየሞች ላይ ሰው ሰራሽ (Artificial turf ) እንዲሁም ቅልቅል ሳሮችን በማምረት እና በማንጠፍ የካበተ ልምድ ካለው የጣሊያኑ ሊሞንታ (Limonta Sport) ጋር የነበረው ንግግር በውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ኩባንያው በስቴዲየሙ ተገኝቶ ዳታ የመልቀም ተግባር ጀምሯል፡፡
ስራውን ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ኃላፊ ኢ/ር አያልነሽ ሐብተማርያም እንደገለፁት በስቴዲየሙ የሚነጠፈው የሳር አይነት ቅልቅል (Hybrid) ሆኖ አይነቱም carpet type እንደሚሰኝ ጠቅሰው ይህም ከ90 – 95 % የተፈጥሮ ሳር እንዲሁም ቀሪው ከ5–10 % ደግሞ አርቴፊሺያል እንደሚሆን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ እግርኳስ ድርሳን ላይ አዲስ ገፅ የሚገልጥና ለስፖርት ቱሪዝም እንዲሁም ለውጪ ግንኙነት ጭምር በጎ ፋይዳ እንደሚኖረው ሃላፊዋ አያይዘው ጠቁመዋል፡፡
በስቴዲየሙ ግንባታ ላይ MNRC በዋና ስራ ተቋራጭነት እንዲሁም ZIAS International Designs PLC በአማካሪነት እየተሳተፉበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ አስታውቋል።