AMN – የካቲት 7/2018 ዓ.ም
ቻይና ከአንድ ሀገር በስተቀር ከሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ወደ ሀገሯ ለሚገቡ ምርቶች የምታስከፍለውን ታሪፍ ከሚያዝያ 23 ጀምሮ እንደምታነሳ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ይፋ ያደረጉት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ዓመታዊው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለተገኙት የአሕጉሪቱ መሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት መሆኑን የሀገሪቱ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ቻይና ቀደም ሲል ለ33 የአፍሪካ ሀገራት የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲ ተግባራዊ ስታደርግ የቆየች ቢሆንም፣ ባለፈው ዓመት ግን ይህንን አሠራር አሕጉሪቱ ካሏት 53 ዲፕሎማሲያዊ አጋሮች ጋር እንደምታሰፋ ገልጻ ነበር።
በዚህም መሠረት ከሚያዝያ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ከኤስዋቲኒ በስተቀር ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የዜሮ ታሪፍ ተፈጻሚ እንደሚሆን ቲአርቲ አፍሪካ ዘግቧል፡፡