“የማቴ እቅድ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ሰጥታ ከምትሰራባቸው ዘርፎች ጋር የተጣጣመ ነው”
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ከሁለት ዓመት በፊት የ45 የአፍሪካ ሀገራት እና የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች በተገኙበት መድረክ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በአፍሪካና ጣሊያን መካከል ባለው ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት የልማት ትብብር ይፋ አደረጉ፡፡ በሮም ይፋ የተደረገው የ“ማቴ እቅድ” (Mattei Plan) የተሰኘው ስትራቴጂካዊ ተነሳሽነት ሲሆን ጣሊያንና አፍሪካ መካከል ዘላቂነት ያለው ልማትና ትብብርን የማጠናከር ዓላማ አለው። የማቴ እቅድ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ ጣሊያን ከተለያዩ ሀገራት ጋር በተለይ በሀይል ዘርፍ ያላት ትብብር ፍትሐዊ፣ የነዳጅ አምራች ሀገራትን ጥቅም ከግምት ያስገባ እንዲሆን ቁልፍ ሚና በተጫወቱት ኢነሪኮ ማቴ ከተባሉ ሰው ስያሜውን እንዳገኘ ጂኦፖለቲካል ሞኒተር ዶት ኮም (Geopoliticalmonitor.com) በገፀ-ድሩ ያሰፈረው መረጃ ያመለክታል፡፡
አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች፣ ሰፊ የሰው ሀይል፣ እምቅ አቅምና ተስፋ ያላት አህጉር ናት፡፡ በዚህም ምክንያት የብዙ ሀያላንና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትን ትኩረት እየሳበች ትገኛለች፡፡ ከአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት አንዷ የሆነችው ጣሊያንም ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራች ትገኛለች፡፡ በማቴ እቅድ ከአፍሪካ ጋር “በእኩል አጋርነት እና በጋራ የማደግ” መርህ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍም እየሰራች ትገኛለች፡፡ ሀገሪቱ ለእቅዱ ፕሮጀክቶች ማስተግበሪያ 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዩሮ በጀት የመደበች ሲሆን በዋናነት ኢነርጂ፣ ግብርና፣ ትምህርትና ስልጠና፣ ጤና፣ ውሃ እና መሠረተ ልማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የጣሊያን – አፍሪካ ጉባኤ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ሁለተኛው ጉባዔ በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ በአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በትናትናው ዕለት ተካሂዷል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የማቴ እቅድ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ሰጥታ ከምትሰራባቸው ዘርፎች ጋር የተጣጣመ ነው፡፡ በሀገር
በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ በተለይ በታዳሽ ሀይል ልማት፣ በግብርና፣ በመሰረተ ልማት፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና በሰው ሀይል ልማት ላይ ከምንሰራቸው ሥራዎች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ትላልቅ የውሃ ሀይል ልማት ፕሮጀክቶችን ከመገንባት አንስቶ ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር በባቡር መስመር፣ በአቬሽንና የኢኖቬሽን ማዕከላትን በመገንባት የምታከናውናቸው ተግባራት በአፍሪካ ለዘላቂ ልማትና ለጋራ እድገት መሰረት የሚጥሉ ናቸው ነው ያሉት፡፡
የጣሊያንና አፍሪካ ትብብር ሚዛናዊና ወደፊቱን የተመለከተ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ስደትን ለማስቆም፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ የአፍሪካን አቅም ለማውጣት፣ በወጣቶችና ቴክኖሎጂ ላይ የሚደረገውን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ በጋራ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የተገቡ ቃሎችን ወደ ተግባር ለመቀየር፣ በጣሊያንና አፍሪካ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ትሰራለች፡፡ በጋራ በመሆንም በጥገኝነት ላይ ሳይሆን በመከባበር፣ በብዝበዛ ላይ ሳይሆን በጋራ ብልጽግና ላይ፣ የወደፊቱን የሚያይ አዲስ ግንኙነት በአፍሪካና አውሮፓ መካከል መፍጠር እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በበኩላቸው፣ በጣሊያንና አፍሪካ ትብብር ባለፉት ሁለት ዓመታት በቢሊዮን ዩሮ የሚቆጠር ገንዘብ በመመደብ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶችን መተግበር ተችሏል፡፡ የተጀመረው ትብብር ሁለቱንም ወገኖች ተጠቃሚ የሚያደርግና በተጨባጭ የሚታይ ነው፡፡ በሀይል ልማት በተለይም በታዳሽ ሀይልና በባዮኢነርጂ ልማት ጣሊያንና አፍሪካ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል ናቸው፡፡ የምግብ ዋስትና ጥረቶችን በመደገፍ፣ የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በመገንባት፣ የጤናውን ዘርፍ ተደራሽነት በማሳደግ፣ በስራ ዕድል ፈጠራና በሌሎች ዘርፎች ጣሊያን ከአፍሪካ ጋር በትብብር እየሰራች እንደምትገኝም ገልጸዋል፡፡
ይህ የጣሊያን- አፍሪካ ጉባኤ ከሮም ውጭ በአፍሪካ ምድር ሲካሄድ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሲሆን ኢትዮጵያ አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር ከማስተሳሰር አንጻር ያላትን ከፍተኛ አቅም እንደሚያሳይ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር)፣ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሰጡት ማብራሪያ፣ ጣሊያንና አፍሪካ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ቅርብ የሆኑ፣ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅያ ሜሎኒ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ግንኙነቱ እየተጠናከረ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡
ጣሊያን ይፋ ባደረገችው በማቴ እቅድ በሚተገበሩ ፕሮጀክቶች 14 የአፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ በሰሜን አፍሪካ እንደ አልጀሪያ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያና ግብፅ እንዲሁም ከሰሀራ በታች ደግሞ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ አይቮሪኮስት እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሀገራት በተለያዩ መስኮች ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው፡፡
በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና አሜሪካ ጥናት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ታሪኩ አብርሃ በተቋሙ ገፀ-ድር ላይ Contemporary Italy- AU Cooperation Efforts: Dynamics and Prospects ahead በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ግንኙነትና ትብብር ያላት ሀገር ናት፡፡
የጣሊያን ዋነኛ የንግድ አጋርና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ናት፡፡ እንደ ዊ ቢውልድ ግሩፕ (ሳሊኒ) ያሉ የግንባታ ኩባንያዎች በግንባታና ሪል እስቴት ልማት በሰፊው እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ በማቴ እቅድም ኢትዮጵያ የጣሊያን ኩባንያዎች በኢንቨስትመንት በስፋት ከሚሰማሩባቸው ዘጠኝ ስትራቴጂክ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ሆና መቀመጧንና ይህም የኢኮኖሚ እድገትንና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚደግፍ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ እና ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔን አጥብቃ የምታራመድ ሀገር እንደመሆኗ፣ የአፍሪካን ጥረት ለማስተባበር እና አጠቃላይ የአህጉሪቱን የልማትና የደህንነት ግቦች ለማሳካት ጣሊያንን እንደ አማራጭ አጋር በመጠቀም በትብብር መስራቷ ምክንያታዊ ነው፡፡ በተጨማሪም ከጣሊያን ጋር የሚደረግ ትብብር ከአውሮፓ ህብረት ማዕቀፍ ውስጥ ካሉ ሌሎች ሀገራት ጋር ተመሳሳይ የፖሊሲ ተነሳሽነቶችን የበለጠ ለማጠናከር መንገድ ይከፍታል። ይህም በአጠቃላይ ኢትዮጵያና አፍሪካ ከአውሮፓ ጋር ለሚኖራቸው የወደፊት የልማት ትብብር እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንደሚፈጥር አቶ ታሪኩ አብራርተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፁ ባወጣው መረጃ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር በመተባበር ሁለተኛውን የጣሊያን-አፍሪካ ጉባዔን በአዲስ አበባ በማስተናገድ በሁለቱ አካላት መካከል ድልድይ ሆናለች ብሏል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ