ቀጣዩ ምርጫና የፓርቲዎች ሚና

You are currently viewing ቀጣዩ ምርጫና የፓርቲዎች ሚና

ለምርጫው ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገልጸዋል

ምርጫ የፖለቲካ መረጋጋትና የሥልጣን ቅቡልነትን የሚወስን ቁልፍ ሥርዓት ነው፡፡ የሰለጠነ ማህበረሰብ መገለጫ እና የዴሞክራሲያዊነት አንዱ መለኪያ እንደሆነም ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አህመድ ሰይድ ይናገራሉ፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝሃነት፣ ዘመን ያስቆጠረ የሀገረ መንግስትነት ታሪክ እና ብዙ ህዝብ እንዲሁም ፍላጎት ባለባቸው ሀገራት አሳታፊ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ ምርጫ ማድረግ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው፡፡

ባለሙያው አክለውም፣ ኢትዮጵያ ሰፊ የማደግ ተስፋና አቅም አላት፡፡ ይህንን ዕድል በአግባቡ ተጠቅሞ የሀገርን ሁለንተናዊ ከፍታ ለማስቀጠል ደግሞ በሀገሪቱ የሚደረጉ ምርጫዎች አሳታፊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጡን ተወዳዳሪ ሆነው በመቅረብ፣ ያላቸውን አማራጭ ሀሳብ ለመራጩ ህዝብ በማቅረብ፣ ስለ ምርጫ ሕግ አባላቶቻቸውም ሆኑ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው በማንቃትና የስልጣን ባለቤት የሆነው መራጩ ህዝብ በካርዱ የሰጣቸውን ድምፅ በጸጋ በመቀበል፣ ለሀገር ሰላምና ዕድገት ከአሸነፈውም ሆነ ከተሸናፊው ፓርቲ ጋር አብሮ በመስራት ለህዝብና ለሀገር፤ ለእውነትና ለዴሞክራሲ መቆማቸውን ሊያስመሰክሩ ይገባል ብለዋል አቶ አህመድ ሰይድ፡፡

ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ካደረጉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መካከል የአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ታፈሰ እንደሚሉት፣ ምርጫን የሚያደርጉ ሀገራት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሀገራቸው እውን እንዲሆን የሚፈልጉ ናቸው፡፡

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማድረግ ጥቂት ጊዜያት ቀርተዋታል፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስታት ለምርጫው ፍትሐዊነት፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊነት ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡

በሌላ በኩል ግን እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ እንደሀገር የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለአብነትም ፓርቲዎች እንዳለፉት ምርጫዎች ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል መሄድ ሳይጠበቅባቸው እጩዎቻቸውን ቢሯቸው ተቀምጠው በዲጂታል መንገድ መመዝገብ የሚችሉበት አሰራር ተዘርግቷል፡፡ ይህም ቀደም ሲል የነበረውን መንከራተትና ተያያዥ ችግር መቅረፍ ችሏል ብለዋል፡፡

ከምንም በላይ ሀገር ይቀድማልና ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን እንወጣለን ያሉት አቶ ሰለሞን፣ ለዚህም አባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችንም በምርጫው ሕግ መሰረት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ እንሰራለን፡፡ እንደ ፓርቲም የስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ የሰጠንን ውጤት በጸጋ እንቀበላለን ብለዋል፡፡

አቶ ሰለሞን አክለውም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግስትና የጸጥታ አካላት እንዲሁም የስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ ቅድሚያ ለሀገር ሰላምና ከፍታ ቦታ በመስጠት ምርጫው አሳታፊ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መስራት እንዳለባቸውም አመላክተዋል፡፡

እንደ ፓርቲ የሀገራችንን ሕግና ደንብ አክብረን ወደ ምርጫ ገብተናል ያሉት የፓርቲው ፕሬዝዳንት፣ ወደ ምርጫ ሲገቡም ለምርጫው ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ እጩዎችን መልምለው በምዝገባ ላይ እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ሂደትም ተወዳዳሪዎች፣ አባላትና ደጋፊዎቻቸው የምርጫ ሕጉን አክብረው እና መራጩ ህዝብ የሚሰጣቸውን ውጤት በጸጋ ለመቀበል የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ፓርቲ ከአመራር ጀምሮ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም ከአባላቶቻቸው ጋር መሰል የግንዛቤ ስራዎች እንደሚከናወኑና ሀገርን ያስቀደመ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እዩኤል ሰለሞን በበኩላቸው፣ ምርጫው አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከፍተኛውን ሚና የሚጫወቱ ተቋማት አሉ፡፡ ይህንንም ተከትሎ በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርሻ አማራጭ ሀሳባቸውን ማቅረብ፣ ይህንን አማራጭ ሀሳብ ማስፈጸም የሚችል አመራር ማፍራት በምርጫ ሰዓትም መሳተፍ ነው፡፡ ምርጫው አሳታፊና ዴሞክራሲ እንዲሆን እንደ አንድ ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ በየትኛውም ሁኔታ ምርጫውን ከሚረብሽ አሉታዊ ከሆነ ድርጊት የመቆጠብ ኃላፊነት አለብንም ብለዋል፡፡

ኢዜማ ከተመሰረተ ጀምሮ ይህ ሁለተኛ የምርጫ ተሳትፎው መሆኑን ያስታወሱት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እዩኤል፣ በመሆኑም እንደ ፓርቲ ሀገሪቱ ያስቀመጠቻቸውን ሕጎች ማክበር ግዴታ እንዳለብን እናምናለን፤ ይህንንም ለአባላቶቻችን በበቂ ሁኔታ አሰልጥነናል፤ በምርጫ ወቅት ልንከተላቸው የሚገቡ ሂደቶችን የተመለከቱ ማንዋሎችንም አዘጋጅተናል ሲሉ አክለዋል፡፡

በተለይም በምርጫ ወቅት ማህበራዊ ትስስር ገጾችን እንዴት መጠቀም አለብን? የሚለውን ጨምሮ የተለያዩ ጠቃሚ ማንዋሎችን በማዘጋጀት አባላት ስርዓት ባለው መልኩ መብታቸውን እንዲጠቀሙና ግዴታቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ተግባራትን እያከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ፓርቲው በሰላማዊና በሕግ አግባብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው፣ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደ ሰለጠነ ፖለቲካ የመፎካከር ዓላማን እንይዛለን፡፡ ፓርቲዎችም ምርጫ ግለሰባዊ ጠብ ሳይሆን የሀሳብ ልዩነት መሆኑን በመረዳት መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፓርቲው ማኒፌስቶ ትናንትን በማከም፣ ዛሬን በሚገባ መጠቀምና መተለም ማዕከል ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ፉክክርና ትብብር ሚዛን እንዲጠበቅ በግንባር ቀደምትነት እንደሚንቀሳቀሱ የገለጹት አቶ አደም፣ በዚህ መሰረትም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሀገራችን ዴሞክራሲን የምናጸናበት እንዲሆን በቁርጠኝነት እንሰራለንም ብለዋል፡፡

ትልማችን የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ ጤናማና ለትብብር የሚመች ማድረግ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀሳብ የሚፎካከሩበት እና የህዝብ ድምፅ ብቻ የስልጣን ምንጭ የሚሆንባት ኢትዮጵያን ማረጋገጥ ነው፡፡

ከዚህ በመነሳትም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልፅግና ፓርቲ ሁለት ዋና ዋና ግቦችን ለማሳካት ይሰራል ያሉት የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊው፣ የመጀመሪያው ምርጫውን ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ተአማኒ በሆነ መልኩ ማከናወን ሲሆን፣ ይህም እንደ ፓርቲ መርህን፣ ሕግን እና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በማክበርና በመተባበር ለስኬታማነቱ በቁርጠኝነት የምንታገልለት፣ በሁሉም ፖለቲካ ተዋንያን እና በህዝባችን ትብብር የምናሳካው እና በኢትዮጵያ መትከል የጀመርነውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የምናሳካበት ወሳኝ ግብ ነው ብለዋል፡፡

ሁለተኛው ግብ ምርጫውን በህዝብ ይሁንታ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማሸጋገር ነው፡፡ ለዚህም ፓርቲው በተግባር ተፈትሾ ብቃቱን ያስመሰከረ ቢሆንም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለአሸናፊነት ለመብቃት በሀሳብ፣ በስትራቴጂ፣ በአሰራርና በአደረጃጀት ዝግጅቱን ያጠናቀቀ መሆኑን ባሳለፍነው ረቡዕ በብልፅግና ፓርቲ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ የዘንድሮው ምርጫ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ልምዶች በተሻለ መልኩ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና አካታች እንዲሆን መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው መራጮች ለምርጫው እንደ ጡብ፣ ተሳታፊ ፓርቲዎች ደግሞ እንደ ማገር ናቸው በሚል የገለጹ ሲሆን፤ የምርጫ አውዱን ለማስፋት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠም መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review