በኮሪደር ልማት የተሰሩ መንገዶች በፈረቃ አራት ጊዜ እየተጸዱ እንደሆነ ተጠቁሟል
አዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳየች ባለው ፈጣን ልማትና ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የትላልቅ ጉባኤዎችና ስብሰባዎች መዳረሻነቷ እያደገ መጥቷል። ለዚህ የግማሽ ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በተገመገመበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የተናገሩትን ለማሳያነት ማንሳት በቂ ነው፡፡ አዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት ከ150 በላይ ትላልቅ ኮንፈረንሶችን አስተናግዳለች፡፡ ዛሬ እና ነገ ደግሞ 39ውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ታስተናግዳለች፡፡
ከተማዋ እንደዚህ ዓይነት ትላልቅ ጉባኤዎችን ስታስተናግድ ከዚህ ቀደም በብዙ መልኩ ወቀሳና ትችት እንዲቀርብባት ምክንያት የነበረው የጽዳቷ ሁኔታ ነበር፡፡ የነበራት የጽዳት ሁኔታ ስሟን፣ ዝናዋን እና ሚናዋን የሚመጥን አልነበረም፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በተለያየ ኃላፊነት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ያገለገሉት አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን እንዳጋሩት፣ የአፍሪካ መሪዎች በህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ በሚመጡበት ጊዜ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አንስቶ የሚሰበሰቡበት አዳራሽ እስኪደርሱ ድረስ፣ ከመንገድ በግራና በቀኝ ያሉት ስፍራዎች በቆርቆሮ ይታጠሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም በመንገዱ ላይ ለእይታ ምቹ ያልሆኑ ቆሻሻ ስፍራዎች ነበሩ፡፡
ትውልድና እድገታቸው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ሜክሲኮ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ እንደሆነ ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ መሀመድ ከድር ይህንን ሀሳብ ይጋራሉ። አካባቢያቸው ከዚህ ቀደም የነበረው ጽዳትና ውበት ብዙ ጉድለቶች ያሉበት እንደነበር ያነሳሉ፡፡ ቆሻሻ በየመንገዱ ተዝረክርኮ፣ ዛፎች ቢኖሩ እንክብካቤ ስለማይደረግላቸው በአረም ተውጠው፣ አጥሮቹ ፈራርሰው፣ ቤቶች የተዥጎረጎረ ቀለም ተቀብተውና ውበታቸው ተደብቆ ይታይ ነበር፡፡
የከተማዋ የጽዳት ጉድለት በገጽታዋ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲፈጥር እንደቆየ እሙን ነው፡፡ ሆኖም በኮሪደር ልማቱ የእግረኛ፣ ሳይክልና የተሽከርካሪ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶችን በመገንባት፣ በአረንጓዴ እፅዋትና አበቦች በማስጌጥ፣ ቤቶችን ተመሳሳይና ደረጃቸውን የጠበቀ ቀለም እንዲቀቡ በማድረግ ከተማዋን እንደ ስሟ አዲስ፣ ውብና ጽዱ ማድረግ ተችሏል፡፡
በሜክሲኮ አካባቢ በመንገድ ዳር ከተሰሩ መቀመጫ ወንበሮች በአንዱ አረፍ ብለው ነፋሻማውን አየር እየተቀበሉ ያገኘናቸው አቶ አበጋዝ ተሰማ፣ አካባቢው ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የሰው ትርምስ ያለበትና ጽዳቱም የተጓደለ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በተለይ የመንገድ ዳር ንግድ በእግር ለመንቀሳቀስ አዳጋች፣ አቧራና ቆሻሻም ተዝረክርኮ ተጥሎ ይታይ ነበር፡፡
በኮሪደር ልማት ሰፋፊ የተሽከርካሪ፣ እግረኛና ሳይክል መንገዶች ተሰርተዋል፤ ዘመናዊ መብራቶች ተተክለዋል፤ ህንፃዎች በቀለም አሸብርቀዋል፤ የመንገድ አካፋዮች፣ በግራና ቀኝ በሳር፣ አበባና ዘንባባ ተውበዋል፡፡ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ስለተገነባም እንደበፊቱ ከቱቦ የሚወጣ የሚሰነፍጥ ሽታ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ “ከተማዋን ውብና ጽዱ ለማድረግ የተሰራውን ስራ አይደለም ማየት የሚችለው የማይችለው እንኳን በዳሰሳ ያውቀዋል፡፡ ይህ ለውጥ የመጣው በአጭር ጊዜ መሆኑ ደግሞ ያስገርማል። እኔ የምኖረው ጎተራ አካባቢ ነው። የስኳር ህመም ስላለብኝ ከጎተራ ወደ ሜክሲኮ መጥቼ እረፍት እያደረኩ በስታዲዬም ቦሌ ወሎ ሰፈር ዞሬ በእግሬ እንቅስቃሴ አደርጋለሁ፡፡ ይህንን የማድረገው መንገዶቹ ምቹና ፅዱ ስለሆኑ ነው” ሲሉ ይመሰክራሉ፡፡
አቶ አበጋዝ አክለውም፤ “ከዚህ ቀደም በውበቱና ጽዳቱ የሚጠቀሰው ቦሌ አካባቢ ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉም ቦሌን መስሏል፡፡ በብዙ አካባቢዎች ወንዞች በመጽዳታቸው እንደ በፊቱ መጥፎ ጠረንና ሽታ የለም፡፡ መንገድ ላይ ቆሻሻ ተጥሎ አይታይም፡፡ አዲስ አበባ አሁን ያላት ገፅታ ከበፊቱ ጋር በምንም ለውድድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ አህጉርና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በኩራት ለማስተናገድ ያስችላታል፤ በርግጥም ብዙ ስብሰባዎች እየተካሄዱባት ነው” ብለዋል፡፡
ከተማዋ በጽዳት ረገድ እያሳየች ያለው ለውጥ በዋና ዋና መንገዶች ብቻ የታጠረ አይደለም፡፡ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ ሰፈሮች ብሎም በሁሉም አካባቢ ነው፡፡ ወይዘሮ አያልነሽ ካሳው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ነዋሪ ናቸው፡፡ ደረቅ ቆሻሻን የሚበሰብስ፣ የማይበሰብስና አደገኛ በሚል በመለየትና በአግባቡ በማስቀመጥ፣ በሳምንት ሁለት ቀን ማክሰኞና አርብ ቤት ለቤት በሚሰበስቡ የጽዳት ሰራተኞች አማካኝነት እንዲወገድ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር በየሳምንቱ ቅዳሜ በመውጣት ከሰፈራቸው ነዋሪ ጋር አካባቢያቸውን ያፀዳሉ፡፡ በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የአካባቢያቸው የጽዳት ደረጃ እየተሻሻለ መምጣቱን ይገልፃሉ፡፡
ሌላኛዋ የሜክሲኮ አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ ጉዳዬ ተሰማም እንዲሁ የአካባቢያቸው የጽዳትና ውበት ሁኔታ እጅግ አስደሳች መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አሁን ሜክሲኮ የማናውቃት እስኪመስለን ድረስ ጽዱና ውብ ሆናለች፡፡ ከመንገዶች ባሻገር መናፈሻዎች ስለተሰሩ ከልጆቼ ጋር በመሆን ቅዳሜና እሑድ በመሄድ እንጫወታለን፤ እንዝናናለን፤ መንፈሳችንን እናድሳለን ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባን ጽዳትና ውበት በመጠበቅ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል የጽዳት ሰራተኞች ይገኙበታል። በከተማዋ ጽዳትና ውበት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚታይ ይናገራሉ፡፡ ወጣት ዘላለም አዲሱ ላለፉት አምስት ዓመታት በሜክሲኮ፣ በስታዲዬም፣ አጣና ተራና የተለያዩ መስመሮች የመንገድ ጽዳት ስራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በከተማዋ መንገዶች ላይ ቆሻሻ በብዛት ይጣል ነበር፡፡ የመንገድ ዳር ንግድን ጨምሮ ከተለያዩ የንግድ ማዕከላትና ቡቲኮች የሚወጣ ቆሻሻ ለጽዳቱ መጓደል የራሱ አበርክቶ ነበረው፤ ህብረተሰቡ ስለጽዳት ያለው ግንዛቤም አላደገም ነበር፡፡
ኮሪደር ልማቱ ለጽዳት ስራው እገዛ እንዳደረገላቸው ወጣት ዘላለም ይናገራል። በአሁኑ ወቅት ከመንገድ ገባ ያሉና በመልሶ ማልማት የፈረሱ አካባቢዎች ላይ ከሚታዩ አንዳንድ የጽዳት መጓደሎች በስተቀር ልማቱ የደረሰባቸው አካባቢዎች ንፁህ፣ ጽዱና ውብ እንደሆኑ ገልጿል፡፡
እነዘላለም ሜክሲኮ አካባቢ ያሉ መንገዶችን በቀን ሦስት ጊዜ በፈረቃ እያፀዱ ይገኛሉ፡፡ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በተሰራው ስራ አሁን ላይ በህገ ወጥ መንገድ ቆሻሻ የመጣል እንቅስቃሴዎች ቀንሰዋል፡፡
ወጣት ዘላለም ሌሊት 10፡30 ሰዓት ከገባ እስከ ቀኑ 5፡30 ሰዓት የጽዳት ስራውን ያከናውናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከተማዋ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እያስተናገደች እንደመሆኗ ለጽዳቱ የበለጠ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ሰዎች በብዛት የሚንቀሳቀሱባቸውን አካባቢዎች ተከታትሎ በማጽዳት፣ የሚለጠፉ ህገ ወጥ ማስታወቂያዎችን በማንሳት፣ በተጠንቀቅ በመቆም እንግዶች በከተማዋ የሚኖራቸው ቆይታ ያማረና አስደሳች እንዲሆን በመስራት ላይ ናቸው፡፡
በመንገድ ጥርጊያ የጽዳት አገልግሎት ላይ ተሰማርተው ያገኘናቸው ወይዘሮ የሽወርቅ መኩሪያም እንዲሁ የዛሬ አምስት ዓመት አዲስ አበባ በነበራት ጽዳትና አሁን ባለው መካከል ከፍተኛ ለውጥ እንደሚታይ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከተለያዩ ተቋማት፣ ከንግድ ቤቶች (ቡቲኮች) የሚጣሉ ቆሻሻዎች የመንገድ ጽዳት ላይ ፈተና እንደነበሩ እሳቸውም በአስተያየታቸው አጠናክረዋል፡፡
የመንገድ ዳር ንግድ እንቅስቃሴ ባለበት አካባቢ ይጣል የነበረው ቆሻሻ ብዙ ስለነበር በስራችን ላይ ጫና ፈጥሮብን ነበር፡፡ ኮሪደር ልማቱ ይህንን ማስቀረት በመቻሉ ከተማዋ ጽዱና ውብ ሆናለች ይላሉ፡፡
አቶ ግርማ ሞገሴ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 የጽዳት አስተዳደር ጽህፈት ቤት የጽዳት ስራዎች አስተባባሪ ናቸው፡፡ የመንገድ ጥርጊያ ጽዳት ሰራተኞች በየቀኑ በሦስት ፈረቃ ከሌሊት 10፡30 ሰዓት እስከ ምሽት ድረስ ይከናወናል፡፡ በህብረት ሽርክና የጽዳት ማህበራት ደግሞ በሳምንት ሁለት ወይም እንደአስፈላጊነቱ ሦስት ጊዜ ከቤት ለቤት ደረቅ ቆሻሻ ይሰበሰባል። በርካታ ተገልጋዮች ያሉባቸው እንደ ሆቴል ካሉ ድርጅቶች በየቀኑ የማንሳት ስራ ይከናወናል፡፡፡ በየቀኑ ማህበረሰቡ ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ እንዲለይና የአካባቢውን ጽዳት እንዲጠብቅ ግንዛቤ ይሰጣል፡፡ በየሳምንቱም ነዋሪው በንቅናቄ አካባቢውን እንዲያፀዳ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በወረዳው ከሜክሲኮ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ ያለው ዋና መንገድ በማሽን በመታገዝ የሚፀዳ ደረጃ አንድ መንገድ ነው፡፡ ሌሎች መንገዶች ደግሞ በሰው ሀይል አማካኝነት ይጸዳሉ፡፡ አቶ ግርማ እንደገለፁት፣ ከዚህ ቀደም ቆሻሻ በየመንገዱ ተጥሎ የሚታይበት ሁኔታ ሰፊ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን በመንገድ ሆነ ከመንገድ ውጪ ቆሻሻ ማየት የማይቻልበት ሁኔታ እየተፈጠረ መጥቷል፡፡ የኮሪደር ልማቱ በተለይ የጽዳት ስራውን በማዘመን ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽህፈት ቤት በሚገኝበት አካባቢ የሚገኝ ወረዳ እንደመሆኑ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጽዱና ውብ በሆነ አካባቢ እንዲካሄድ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ጽዳት እንዲጠብቅ ግንዛቤ በመፍጠርና መንገዶች ሁሌም ንፁህ ሆነው እንዲገኙ የዘወትር ክትትል እየተደረገ ይገኛል፡፡
እንደ ከተማ ምን እየተሰራ ነው?
አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ በዓመት አንድ ጊዜ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ጨምሮ የተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ጉባኤዎችና ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ውብና ጽዱ እንድትሆን ሰፋፊ ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ በአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የዋና ዳይሬክተር ዋና አማካሪ ወይዘሮ ሀዳስ ኪዱ ይገልፃሉ፡፡
መንገዶች አካባቢ ያሉ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ (ደስት ቢን) በየቦታው መኖራቸውን የማረጋገጥ፣ የተበላሹትን የመጠገንና የማስተካከል ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ጽዳታቸውን የጠበቁ፣ እንግዶች በብዛት የሚንቀሳቀሱባቸውን ቦታዎች በመለየት የሚያርፉባቸው ሆቴሎችና የእንግዳ ማረፊያዎች ጽዱና ውብ እንዲሆኑ የሚመነጨውን ቆሻሻ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ እንዲነሳና እንዲጓጓዝ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ዋና አማካሪዋ እንደሚገልፁት፣ የኮሪደር ልማት የተከናወነባቸውም ሆነ ያልተከናወነባቸው መንገዶች ጽዱና ውብ ሆነዋል፡፡ እናቶች፣ ሴቶችና ወጣቶች ሌሊት ከቤታቸው 10፡00 ሰዓት በመነሳት እስከምሽቱ 1፡30 ሰዓት ድረስ በአራት ፈረቃ (እንደየመንገዱ ሁኔታ የሚለያይ ሆኖ) ያፀዳሉ፡፡ የፅዳት ስራው የመብራት ችግር እንደበፊቱ ባለመኖሩ ከሌሊት ጀምሮ እስከ ማታ ይሰራል፡፡ ከዚህ በፊት ከነበረው ሦስት ፈረቃ በተጨማሪ አንድ ተጨምሮ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በኮሪደር ልማት የተሰሩ መንገዶች አንደኛ ደረጃ የሚባሉ ሲሆን በፈረቃ አራት ጊዜ ይጸዳሉ፡፡
ቆሻሻ ከቤት ለቤት የመሰብሰብ ስራ ወደ ማታ ባለው ክፍለ ጊዜ እንዲዛወር ተደርጓል፡፡ የውስጥ ለውስጥ መብራቶች እንዲኖሩ በመደረጉ ስራውን ያለምንም ችግር ለማከናወን አስችሏል። በተጨማሪም ደረቅ ቆሻሻ በባህሪው ሽታ ስላለው ይህንን ለመቀነስ ማታ አየሩ ቀዝቀዝ በሚልበት፣ የትራፊክ እንቅስቃሴ በሚቀንስበት፣ ያደጉ ሀገራት ውጤታማ አሰራር በመሆኑ ተሞክሮን በመውሰድ እየተሰራበት እንደሆነ ወይዘሮ ሀዳስ አስረድተዋል፡፡
እንግዶች ቢመጡም ባይመጡም ከተማዋ ዘወትር ጽዱ እንድትሆን ስርዓት ተዘርግቷል፡፡ በተጨማሪም እንደ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተለያየ ጉባኤ ሲካሄድ አዲስ አበባ ጽዱና ውብ ሆና እንድትሆን በተለየ ሁኔታ በንቃት ተሰርቷል፡፡ እንግዶች በሚያልፉባቸውና በሚያንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች አዋኪ የሆኑ ከግንባታ ጋር በተያያዘ መንገዶች ላይ ተረፈ ምርቶች፣ ቁፋሮዎች ካሉ ቶሎ እንዲነሱና እንዲስተካከሉ የማድረግ ስራ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በትብብር ስለመሰራቱ ወይዘሮ ሀዳስ ያነሳሉ፡፡
ድሮ እንግዶች ከየት ተነስተው የት እንደሚቆዩ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት እንግዶች በከተማዋ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተወሰነ አካባቢ የተገደበ አይደለም የሚሉት ዋና አማካሪዋ፣ በኮሪደር እና ወንዝ ዳርቻ በርካታ አካባቢዎች ለምተዋል፡፡ አዳዲስ መናፈሻዎች፣ ፓርኮችና ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻዎች ስላሉ ሰፊ አካባቢዎች ላይ ይንቀሳቀሳሉ፡፡
ለምሳሌ የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጀምሮ እስከ የህብረቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ የሚገኝበት ሜክሲኮ፣ ሆቴሎች በአብዛኛው በሚገኙባቸው ካዛንቺስ ያርፋሉ፤ ወደ ሽሮ ሜዳ ለግብይት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ እንጦጦ ፓርክ ለጉብኝት ይሄዳሉ፡፡ የወንዝ ዳርቻ ልማቶችን ይጎበኛሉ፡፡ ወደ አዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልም ይሄዳሉ፡፡ ከዚህ አኳያ እንግዶች ይንቀሳቀሱባቸዋል ተብለው የሚታሰቡ አካባቢዎች የበለጠ ጽዱና ውብ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው፡፡ የሚሰበሰብ ቆሻሻ 24 ሰዓት ሳይሞላ በቶሎ እንዲነሳ በቅርብ ክትትል እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ ሀዳስ እንደገለፁት፣ የኮሪደር ልማቱ የጽዳት ስራውን በማቃለል ትልቅ እፎይታ ፈጥሯል፡፡ ሰፋፊ የተሽከርካሪ፣ የሳይክል እና እግረኛ መንገድ፣ በየቦታውም የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች በማካተት ጽዱ ሆነው ተገንብተዋል፡፡ ማህበረሰቡ ቆሻሻን በአግባቡ እንዲያስወግድ፣ አንዳንድ በቸልተኝነት ቆሻሻ የሚጥሉ ሲገኙ ራሱ ማህበረሰቡ “ለምን ትጥላላችሁ?” በማለት የሚጠይቅበትና ባለቤት የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ዋና አማካሪዋ እንደሚሉት፣ በከተማዋ ከዚህ ቀደም አብዛኛው የንግድ እንቅስቃሴዎች በእግረኛ መንገዶች ላይ ይካሄዱ ስለነበር የጽዳት ሰራተኞች መሀል አስፋልት ውስጥ ራሳቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ በመግባት ያፀዱ ነበር፡፡ አሁን ግን ርቀታቸውን ጠብቀው፣ ከሰውና የንግድ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ከሚፈጠር ግፊያና ተፅዕኖ ነፃ ሆነው የሚያጸዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
አዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገች የመጣች ሲሆን፤ በዚያው ልክ ደረቅ ቆሻሻ የመሰብሰብ፣ የማጓጓዝና የማስወገድ አገልግሎቱን ለማዘመን እየተሰራ ነው። የመንገድ ጽዳት ስራው ከእናቶች ትከሻ ተላቅቆ በቴክኖሎጂ ተደግፎ፣ በአውትሶርስ (በግል የጽዳት ስራ የተሰማሩ ድርጅቶች) እንዲሰጥ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የአንደኛ ደረጃ (ቪአይፒ) መንገዶች (ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጀምሮ እስከ ብሔራዊ ቤተ መንግስትና ሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች የሚገኙ) ቆሻሻ በሚያነሱ መኪናዎች (Sweeper Cars) በመታገዝ እየጸዱ መሆኑን ወ/ሮ ሀዳስ ተናግረዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ