የመዲናዋ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች

You are currently viewing የመዲናዋ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች

በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መርሃ ግብር መቅረባቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ከተሰናዱት መካከልም የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ እና የመጽሐፍት ውይይት ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጽሐፍ

የአንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ግለ-ታሪክ መጽሐፍ ከሰሞኑ ለንባብ ይበቃል፡፡ “እንዲህም ተኑሯል” የሚል ርዕስ ያለውና በ550 ገፆች የተቀነበበው የዚህ መጽሐፍ ምረቃ ዛሬ በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት (ወመዘክር) አዳራሽ ከቀኑ 8 ሰዓት ይካሄዳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ምክንያት መራዘሙ ተገልጿል፡፡ አበራ ለማ ከሀገራችን ገጣሚያንና አጫጭር ልብ-ወለድ ጸሐፊዎች አንዱ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ጥናት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቋል።

አበራ፣ በ1967 ዓ.ም  “ኩል ወይስ ጥላሸት” እንዲሁም  በ1974 ዓ.ም “ሽበት” የተሰኙ የግጥም መድብል ስራዎችን ለህትመት አብቅቷል፡፡ ከዚያም “ሕይወትና ሞት” የተሰኘ የአጫጭር ልብ-ወለዶች ስብስብ፣ ቀጥሎም “ሞገደኛው ነውጤን” አሳትሟል፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ስራዎችንም በግሉና በጋራ  አበርክቷል፡፡

የፎቶ ግራፍ  አውደ ርዕይ

ኢትዮጵያ በ1920ዎቹ በጀርመናዊ ዲፕሎማት “እይታ” በሚል ርዕስ የፎቶ ግራፍ ዓውደ ርዕይ እየታየ ነው፡፡ ዓውደ ርዕዩ በወቅቱ በኢትዮጵያ የጀርመን መልዕክተኛ በነበሩት በሚስተር ፍሪትዝ ዊይስ (Fritz Weiss) እና ባለቤታቸው ሄድዊግ የተቀረጹ 51  ፎቶ ግራፎች እና ቪዲዮዎች የቀረቡበት ነው፡፡ እነዚህ  ምስሎች ከቀድሞዋ አዲስ አበባ ከተማ እይታዎች ጀምሮ እስከ ደመቅ ያሉ ባህላዊ በዓላት እና አስደናቂ ገጠራማ ስፍራዎች ድረስ የያኔውን የኢትዮጵያ የዕለት ተዕለት ሕይወት በቅርበት ያሳያሉ ተብሏል፡፡ አውደ ርዕዩ እየታየ የሚገኘው ሃያት ሬጀንሲ በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ሲሆን በመጪው ሰኞ ይጠናቀቃል፡፡

ፊልም

“ይቅር ባይ” የተሰኘውና በዛክ ፒክቸርስ ተዘጋጅቶ በኤልያና ኢንተርቴይመንት የቀረበው  የዘካርያስ ወንድይፍራው  አዲስ ፊልም  ከትናንት ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት በተመረጡ ሲኒማ ቤቶች እየተመረቀ ይገኛል።

ፊልሙ ትናንት  ከኤግዚቢሽን ማዕከል ጎን በሚገኘው አዲሱ ሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር አዳራሽ በቀይ ምንጣፍ ስነ- ስርዓት የፊልም አፍቃሪያን፣ የኪነ – ጥበብ ባለሙያዎች እና ሚዲያዎች በተገኙበት የተመረቀ ሲሆን፤ ነገም በተመረጡ ሲኒማ ቤቶች መመረቁን ይቀጥላል፡፡ በፊልሙ ላይ ካሳሁን ፍስሐ (ማንዴላን) ጨምሮ አንጋፋና ወጣት ተዋናያን ተሳትፈውበታል፡፡

 ሙዚቃ

የወጣት ሶሲ ግርማ አዲስ ሙዚቃ ለአድማጭ ተመልካች ይፋ ሆነ። “አይጣል” የተሰኘው ይህ የፍቅር ሙዚቃ ትናንት ምሽት በናሆም ሬከርድስ አማካኝነት ለህዝብ ደርሷል፡፡ በዚህ ስራ በግጥም ፍሬዘር አበበወርቅ፣ ዜማ ብሩክ ጃኔ እና በሙዚቃ ቅንብር ብሩክ ተቀባ ተሳትፈውበታል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review