ስፖርቱ በአጀንዳ 2063 ዓይን

You are currently viewing ስፖርቱ በአጀንዳ 2063 ዓይን

አጀንዳ 2063 አፍሪካን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ የማድረግ ግብን ያነገበ የ50 ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ነው። አህጉሪቱ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ዘርፎች የበለፀገችና አንድነት ያላት እንድትሆን ግብ ያስቀመጠም ነው። በዚህ ግዙፍ ዕቅድ ውስጥ ስፖርት አህጉራዊ ትስስርን የሚያፋጥን፣ ሰላምን የሚያሰፍንና በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያመነጭ ስትራቴጂካዊ ዘርፍ ተደርጎ ተለይቷል።

ስፖርት በግጭት ቀጣናዎች ውስጥ እንደ ‘ለስላሳ ዲፕሎማሲ’ በማገልገል፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማጠናከርና ወጣቶችን ከአመፅ ተግባራት ማራቅን አልሞ ወደ ተግባር ስለመግባቱ የሕብረቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከስፖርት ኢንዱስትሪው በአህጉሪቱ ለሚገኙ ከ5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) እስከ አንድ በመቶ የሚደርስ ድርሻ እንዲያበረክት ማድረግ በአጀንዳ 2063 የስፖርቱ መስክ ቁልፍ የፖሊሲ ግቦች ተደርገው የተቀመጡ ዋና ዋና ግቦች መካከል ተጠቃሽ ነው።

የአፍሪካ ሕብረትም ስፖርት የፖለቲካ ልዩነቶች የማይገቡበት ‘ገለልተኛ ሜዳ’ በመሆኑ፣ በጦርነትና በትርምስ ውስጥ ለነበሩ ሀገራት ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እንደ ትልቅ መሣሪያ እየተገለገለበት ይገኛል። በሌላም በኩል ሕብረቱ ስፖርትን ‘ፓን-አፍሪካኒዝምን’ ለማጠናከር እየተጠቀመበት ሲሆን፣ እንደ አፍሪካ ዋንጫና የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ያሉ መድረኮች ከአምስት ቢሊዮን በላይ ለሚሆኑ የዓለም ሕዝቦች የአፍሪካን አንድነትና ብዝሃነት የሚያሳዩ ትዕይንቶች ሆነው እንዲያገለግሉ እየተሠራ ነው።

የቀድሞው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት “ስፖርት ለአፍሪካ ሰላም እና ለልማት ሥራዎቻችን እንደ ድልድይ ያገለግላል። አጀንዳ 2063ን እውን ለማድረግ ወጣቶቻችንን በስፖርት ማስተሳሰርና የአህጉሪቱን አወንታዊ ገጽታ ለዓለም ማሳየት አለብን” ማለታቸውም ለዚሁ ነው፡፡

በኬፕ ታውን ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ስፖርት በአፍሪካ ውስጥ ከፖለቲካዊ ድንበሮች በላይ የጋራ ማንነትን የመፍጠር አቅም አለው። ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ስፖርት በተለይ በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረቱ ግጭቶችን በማለስለስ ረገድ ወደር የሌለው መሣሪያ ነው። አህጉሪቱ የምታሰናዳቸው ስፖርታዊ መድረኮች ደግሞ አፍሪካዊያን በብሔርና በቋንቋ ሳይከፋፈሉ ለአህጉራቸው ኩራት እንዲሰማቸው ያደርጋሉ። ሕብረቱ ስፖርትን እንደ ድልድይ በመጠቀም፣ የፓስፖርት አገልግሎት ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት በስፖርት አማካኝነት የልብ አንድነትን ለማምጣት እየሠራ ነው።

ስፖርትን ከማህበራዊ ፋይዳው ባለፈ እንደ ኢንዱስትሪ የሚመለከተው አጀንዳ 2063፣ ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ እንደመሆኑ አፍሪካ ከዚህ ተጠቃሚ እንድትሆን እየሠራ ይገኛል፡፡ በኬፕታውን ዩኒቨርሲቲም ስፖርት ለልማት (Sport-for-Development) በሚል ርዕስ የተደረጉ የኢኮኖሚ ትንታኔዎች፣ አፍሪካ የስፖርት ኢንዱስትሪዋን በአግባቡ ብትመራ የአህጉሪቱን ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 5 በመቶ እስከ 2 በመቶ መካከል የማሳደግ አቅም እንዳለው ይጠቁማሉ።

አጀንዳ 2063 ስፖርትን ለሰላምና ለአንድነት እንዲውል ያስቀመጠው አቅጣጫ እንዲሳካ አባል ሀገራት በስፖርት ፖሊሲዎቻቸው ላይ ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እንደዚሁም ዘመናዊ ስታዲየሞችና የስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዲገነቡ ማበረታታት፣ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ኩነቶችን በማስተናገድ የውጭ ምንዛሬና የሥራ ዕድል መፍጠር እና አፍሪካዊያን አትሌቶችና የእግር ኳስ ተጫዋቾች የአህጉሪቱ ‘አምባሳደሮች’ በመሆን የአፍሪካን ስም እንዲገነቡ ማድረግ የሚሉ ግቦችም ይገኙበታል።

የአፍሪካ ሕብረት ስፖርትን እንደ መደበኛ የፖሊሲ አካል በመቅረጽ ረገድ ላለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት ተጨባጭ ስኬቶችን አስመዝግቧል። እነዚህ ስኬቶች ከስታዲየም ባሻገር በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች የታዩ ናቸው። ሕብረቱ ስፖርትን በግጭት ቀጣናዎች ውስጥ እንደ የእርቅ መሣሪያ በመጠቀም ረገድ ውጤታማ ሥራዎችን ሠርቷል።

በደቡብ ሱዳን እና በሊቢያ በነበሩ የውስጥ ግጭቶች ወቅት፣ ሕብረቱ ከቀጣናዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የስፖርት ውድድሮችን በማዘጋጀት ተፋላሚ ወገኖች በሰላም እንዲነጋገሩ መድረክ አመቻችቷል። በተለይም ‘የአፍሪካ ሰላም ቀን’ (International Day of Peace) ሲከበር የሚደረጉ የወዳጅነት ጨዋታዎች፣ ወጣቶች ከጠመንጃ ይልቅ እግር ኳስን እንዲመርጡ የማድረግ ትልቅ ሥነ-ልቦናዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል።

የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት ትልልቅ የዓለም ስፖርታዊ ኩነቶችን በብቃት እንዲያስተናግዱ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ በማድረግ የአህጉሪቱን ገጽታ ቀይሯል። እ.ኤ.አ በ2010 በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ሕብረት ‘የአፍሪካ ዋንጫ ነው’ ብሎ በጋራ የደገፈውና ያስፈጸመው ትልቅ ስኬት ነበር። ይህ ዝግጅት አፍሪካ ግዙፍ መሠረተ ልማቶችን የመገንባትና በዓለም አቀፍ ደረጃ በብቃት የማስተዳደር አቅም እንዳላት ለዓለም ያረጋገጠበት የታሪክ ምዕራፍ ነው።

ሕብረቱ ስፖርት በዘፈቀደ ሳይሆን በሕግና በሥርዓት እንዲመራ የሚያደርጉ ተቋማዊ ሥራዎችን አከናውኗል። ‘የአፍሪካ ስፖርት ልማት ፖሊሲ ማዕቀፍ’ (Architecture for Sport in Africa) መጽደቁም አንዱ ስኬት ሲሆን፣ ይህም ሀገራት የስፖርት በጀት እንዲመድቡ፣ ዶፒንግን (አበረታች መድኃኒት) በጋራ እንዲከላከሉ እና በስፖርቱ ውስጥ ያለውን ሙስና እንዲታገሉ መንገድ ከፍቷል። እንደ ዋዳ (World Anti-Doping Agency) ካሉ ድርጅቶች ጋር በጋራ መስራቱ የአፍሪካ አትሌቶች በዓለም መድረክ ተዓማኒነት እንዲኖራቸው አድርጓል።

በተለምዶ የወንዶች ብቻ ተደርጎ ይወሰድ የነበረውን ስፖርት፣ ሕብረቱ የሴቶች ማብቂያ መሣሪያ (Empowerment) እንዲሆን አድርጓል። የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ (WAFCON) በየዓመቱ በጥራትና በተመልካች ቁጥር እያደገ መምጣቱ የሕብረቱ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነት ስኬት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን፣ ይህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን ሴት ልጆች በራሳቸው እንዲተማመኑና ከስፖርት ባለፈ በትምህርትና በንግድ ውጤታማ እንዲሆኑ አነሳስቷል።

ይህ በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው ግዙፍ ስፖርታዊ ኩነት፣ የአፍሪካ ሕብረት አህጉራዊ አንድነትን በተግባር የሚያሳይበት መድረክ ነው። በቅርቡ በጋና የተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች፣ ከ50 በላይ ሀገራት የተሳተፉበትና በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ባህላቸውንና ስፖርታዊ ጨዋነታቸውን የተለዋወጡበት ነበር። ይህ መድረክ አፍሪካዊያን በራሳቸው ዳኞች፣ በራሳቸው ሜዳና በራሳቸው ደንብ የሚወዳደሩበት ‘የአፍሪካዊያን ኦሎምፒክ’ ተደርጎ ይወሰዳል።

ሕብረቱ ሀገራት በስፖርት መሠረተ ልማት ላይ እንዲያተኩሩ ባደረገው ግፊት፣ በአህጉሪቱ የታዩ የኢኮኖሚ ስኬቶች መካከል ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ በአጀንዳ 2063 መሪ ዕቅድ መሠረት ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች በአፍሪካ ተገንብተዋል።

የስፖርት ዘርፉ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ለሚገኙ ከ5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የስፖርት ቱሪዝም ለአፍሪካ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) በአማካይ 0 ነጥብ 5 በመቶ እስከ 1 በመቶ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ የአፍሪካ ልማት ባንክ መረጃ ያመላክታል፡፡

የአጀንዳ 2063 ስፖርት ነክ ግቦችን የሚከታተል የአፍሪካ ሕብረት የስፖርት ምክር ቤት በየጊዜው የሚያወጣቸው ‘Status of Sport in Africa’ የተሰኙ ሪፖርቶች ቁጥራዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት 85 በመቶ የአፍሪካ ወጣቶች ስፖርትን እንደ ‘ብሔራዊ አንድነት’ መግለጫ ያዩታል። 60 በመቶ የሚሆኑት በግጭት ቀጣና የሚኖሩ ወጣቶች እንደዚሁ በስፖርት ተሳትፎ ምክንያት ከዓመፅ ተግባራት መራቃቸውን ይገልጻሉ። ባለፉት 7 ዓመታት ሴቶች በስፖርት አመራር ላይ ያላቸው ተሳትፎ 30 በመቶ ጨምሯል።

ለስላሳ ኃይል ማለት አንድ ሀገር ወይም አህጉር በኃይል ወይም በገንዘብ ሳይሆን፣ በባህል፣ በስፖርትና በዕሴቶቹ አማካኝነት የሌሎችን ልብ የመግዛትና ተፅዕኖ የማሳደር አቅም ነው። ለዚህም ነው አጀንዳ 2063 ስፖርትን የአፍሪካዊያን ማንነት መገለጫና የአንድነት ማሰሪያ አድርጎ እየሠራበት የሚገኘው።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review