AMN- የካቲት 8/2018 ዓ.ም
በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጡት እንግዶች ስለ አዲስ አበባ ከተማ ልማትና ፈጣን እድገት ያዩትን አስገራሚ አስተያየት ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜም ሆነ ለተከታታይ ጊዜያት ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጡ የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ ያለውን ልማት በአድናቆት ተናግረዋል፡፡
ለስድስተኛ ጊዜ አዲስ አበባን የጎበኙት ሱዳናዊው ተሳታፊ፣ ከተማዋ በልማት ስራዎች ይበልጥ አምራና ተውባ መጠበቋን በአድናቆት ገልጸዋል።
በሁሉም የመዲናዋ አቅጣጫዎች አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን መታዘባቸውን የገለጹት አስተያየት ሰጪው፤ አዲሶቹ መንገዶችና የጎዳና መብራቶች ተዳምረው ለአዲስ አበባ ልዩ ውበት ማልበሳቸውን በአድናቆት ተናግረዋል።

ሌላኛዋ ከዛምቢያ የመጡት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው በአደስ አበባ ከተማ የተመለከቱትን መሰረተ ልማት እጅግ አድንቀዋል፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ የመሠረተ ልማቶች የጥራት ደረጃ እጅግ አስገራሚ መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጪዋ፣ የከተማዋን ውበትና ምቹነት ከዱባይ ጋር በማነፃፀር “አሁን ላይ ያለሁት አዲስ አበባ ሳይሆን ዱባይ ውስጥ ነው የሚመስለኝ” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወኑ የልማት ስራዎች መደነቃቸውንና መደሰታቸውን የገለጹት አስተያየት ሰጪዋ፣ ከእነዚህ አስደናቂ ተግባራት በስተጀርባ ያለውን አፍላቂ አእምሮ ማድነቃቸውንም አክለው ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተሰራው የልማት ስራ ከተማዋን በእጅጉ እየለወጣት መሆኑን የተናግሩት ደግሞ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር ፌዴሬሽን የመጡት አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ወንዞች ከመቼውም ጊዜ በላይ ንጹህ መሆናቸውን የገለጹት አስተያየት ሰጪው፤ በወንዞቹ ዳርቻ በተገነቡት ምቹ የእግረኛ መንገዶች ላይ ያለምንም እንግልት መጓዝ መቻላቸውን በደስታ ተናግረዋል።

አዲስ አበባን ከተለያዩ መንግሥታት የአስተዳደር ዘመናት ጀምሮ እንደሚያውቋት የገለጹት ዝምባብዌያዊው አስተያየት ሰጪ፤ ከተማዋ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ያስመዘገበችው አስደናቂ የልማት ስኬት ከአመራር ለውጥ ጋር የተቆራኘ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በአዲስ አበባ ተከማ እየታየ ያለው የልማት ለውጥ ትልቅ ተፅዕኖ የፈጠረ መሆኑን እንደተመለከቱም ገልጸዋል፡፡
ከኢስዋቲኒ የመጡት የጉባኤ ተሳታፊ በሰጡት አስተያየት ደግሞ ከዚህ በፊት ብዙ ሰዎች አዲስ አበባን መርተዋታል ግን አሁን እየታየ እንዳለው አይነት የልማት ለውጥ ማምጣት አልቻሉም ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ግን ከተማዋን በትክክል የሚመራትና ወደ ልማት ጎዳና እያሻገራት ያለ መሪ ማግኘቷን በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡
በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የታደሙት ተሳታፊዎች፣ የአዲስ አበባን ገጽታ ለመቀየር የታየውን የአመራር ቁርጠኝነት አድንቀዋል። አክለውም በመዲናዋ የተከናወኑት የልማት ስራዎች ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሊቀስሙትና ሊከተሉት የሚገባ ታላቅ ተሞክሮ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።
በአስማረ መኮንን