AMN የካቲት 8/2018
ከነገ ጀምሮ የሚገባውን ዐቢይ ጾም ምዕመናን የተቸገሩትን በማገዝ መጾም እንደሚጠበቅባቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አስገነዘቡ።
በነገው ዕለት የሚጀመረውን የ2018 ዓ.ም የዐቢይ ጾም ሱባዔ በማስመልከት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም፤ የመንፈስ ፍሬዎች የሆኑትን ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትን፣ ርኅራኄንና፣ ሃይማኖትን ማስፈን ምርጫችን ልናደርግ ይገባል ብለዋል።
ቤተክርስቲያንም እንድንጾም የምታስተምረን እነዚህን ለመተግበር ጾም ፍቱን መሳሪያ ሆኖ ስለሚገኝ ነው ሲሉም አስረድተዋል።
ከዚህ አንጻር የጾም ዓላማውና ግቡ ጽኑዕ ሃይማኖትን፣ እውነተኛ ፍቅርን፣ ዘላቂ ሰላምን፣ ልባዊ አንድነትን፣ የማይናወጥ ፍትሕንና እኩልነትን ወሰን የሌለው ርኅራኄን በውስጣችን ብሎም በዓለማችን ማሥረጽ እንደሆነ በውል መገንዘብ አለብን ብለዋል።
በመሆኑም ምዕመናን የተራቡትን በማጉረስ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የተጣሉትን በማስታረቅ ጾሙን እንዲጾሙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።