AMN – የካቲት 9/ 2018
39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የተሳተፉት እንግዶች ወደ አዲስ አበባ በመጡ ቁጥር የሚመለከቱት ለውጥ አስደናቂ መሆኑን ገለጹ፡፡
ለሁለት ቀናት የተካሄደው የሕብረቱ ጉባኤ በትናንትናው ዕለት ተጠናቅቋል፡፡ በፈጣን ለውጥ ውስጥ የምትገኘውና በየጊዜው አዳዲስ ነገር አከናውና የምትጠብቀው አዲስ አበባ ለብዙዎቹ ታዳሚያን ግርምትን የሚፈጥር ሆኗል፡፡
ከጋምቢያ የመጣው ኦማር ባንዴ የተሰሩት መንገዶች “ወደ አፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት የምናደርገው ጉዞ በጣም ጥሩ ሆኗል።” ሲል እቅስቃሴን ቀልጣፋ እንዳደረጉ ይገልጻል፡፡

ያለ ማቋረጥ 24/7 የሚካሄደው ግንባታ እንዳስደነቃቸው ነው እንግዶቹ የሚገልጹት፡፡ ደጋግመው የመጡ እንግዶች ከዚህ በፊት ባልነበረ መልኩ የዘመነ ከተማ እየተገነባ እንደሆነ መታዘባቸውን ይናገራሉ፡፡
ባለፉት 15 ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ መመላለሳቸውን የሚናገሩት አንጎላዊው ጆሽ ገርዴዢ በአዲስ አበባ በርካታ ለውጦች መኖራቸውንና አሁን ላይ ያደገች ዘመናዊ ከተማ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
በርካታ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላት መሆኗን በመጥቀስ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለዜጎች ህይወት መለወጥ፣ ለእንግዶች ጭምር የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ እየሰሩ በሚገኙበት ስራ በእጅጉ ኩራት እንደተሰማቸው ነው ጆሽ ገርዴዢ የተናገሩት፡፡
ጋምቢያዊው ኦማር ባንዴ የሆቴል አገልግሎቱ ጥሩ መሆኑንና መልካም መስተንግዶን እያገኙና ህይወት ቀላል እንደሆነችላቸው ገልጸዋል፡፡ አዲስ አበባ ለበርካታ አቻ ከተሞቿ ምሳሌና መነሳሳት መሆን የምትችል መሆኗንና ተሞክሮ የሚቀስሙባት እንደሆነች ነው እንግዶቹ የሚጠቅሱት፡፡ ከኮትዲቯር የመጣችው ኬቲ ሎሁ በበኩሏ በአዲስ አበባ እየተመለከትነው የሚገኘው ለውጥ የማይታመን ነው ትላለች፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከተማዋ በሚያስገርም ሁኔታ ስትለወጥ እየታዘብኩ ነው የምትለው ኬቲ ሎሁ ፣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በፍጥነት መጠናቀቃቸው እንዳስገረማት አልሸሸገችም፡፡
ይህ ለቆምንለት አላማ መሳካት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ መሆን የሚችል እንደሆነ ነው ኳትዲቯራዊቷ ኬቲ የገለጸችው፡፡ ኢትዮጵያውያን ብርቱ ህዝቦች ናቸው ሲሉ የገለጹት እንግዶቹ ዕቅድን ወደ ተግባር የመለወጥ አቅምን አድንቀዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ በራስ አቅም መፈጸማቸው ደግሞ ትክክለኛው መንገድና አፍሪካውያን ሊማሩበት የሚገባ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
አፍሪካ ልትመስል የሚገባት ለዜጎቿ አስፈላጊውን መሰረተ ልማት ያሟላች፣ የምጣኔ ሀብታዊ እድገቷን ያረጋገጠች በመሆኑ ፣ አፍሪካውያን መሰረተ ልማት ላይ እንዲሰሩ መነሳሳት እደሚሆን እንግዶቹ ገልጸዋል፡፡
ታደሰ ሽፈራው