ምርጫው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሚጣልበት እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ

You are currently viewing ምርጫው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሚጣልበት እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ
  • Post category:ፖለቲካ

AMN – የካቲት 10/2018 ዓ.ም

ምርጫው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሚጣልበትና የሕዝብ ሉዓላዊነት በተግባር የሚረጋገጥበት እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ማስተዋወቂያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ ምርጫው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሚጣልበትና የሕዝብ ሉዓላዊነት በተግባር የሚረጋገጥበት እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርጫው ፍፁም ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ፓርቲው ያለውን ቁርጠኝነት ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ቀደም ባሉ ዘመናት የሕዝብ ሉዓላዊነትና የሐሳብ የበላይነት ሳይከበር በመቆየቷ ለነበረባት የዴሞክራሲ እጥረት፣ ይህ 7ኛው ምርጫ የሕዝብ ድምፅ የሚከበርበትና ፍትሐዊነት የሚነግሥበት እንዲሆን ሙሉ ዝግጅት መደረጉንም በመድረኩ እየተገለጸ ነው።

ይህም ሀገሪቱን ወደ ተምሳሌትነት የማሸጋገር ጉዞ አካል መሆኑ ተመላክቷል።

የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው፣ ፓርቲው ሀገር በቀል በሆነው “የመደመር” እሳቤ በመመራት በቃሉ ታምኖ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች አቅርበዋል።

ክልሉም ሆነ ሀገሪቱ ከተስፋ ብርሃን ወደ ሚጨበጥ ብርሃን መሸጋገራቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ይህንን የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ግልጽ ራዕይ ዕውን ለማድረግ፣ በዕውቀትና በተግባራዊ ውጤታማነት የታጀበ አዲስ ማኒፌስቶ ለሕዝብና ለአባላት ይፋ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በመድረኩ ላይ በትብብርና በፉክክር መካከል ያለውን ሚዛን የጠበቀ ዴሞክራሲ የመገንባት አስፈላጊነት በሰፊው እየተዳሰሰ ይገኛል።

በሁሉም መስክ የክልሉን ፀጋዎች በማልማት የጠንካራ ሀገር ተምሳሌትነትን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ የማይተካ ሚና እንዳለው እየተገለጸ ሲሆን፣ የመደመር፣ የብልፅግናና የልዕልና ትርጉም ያለው የፓርቲው መለያ “የስንዴ ነዶ” ምልክትም እየተዋወቀ እንደሚገኝ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review