በመዲናዋ ብክለት ከሚያስከትሉ የፕላስቲክ አይነቶች መካከል የፕላስቲክ ከረጢቶች 46 በመቶውን እንደሚይዙ ተገለጸ

You are currently viewing በመዲናዋ ብክለት ከሚያስከትሉ የፕላስቲክ አይነቶች መካከል የፕላስቲክ ከረጢቶች 46 በመቶውን እንደሚይዙ ተገለጸ

AMN- የካቲት 10/2018 ዓ.ም

አንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮች ላይ የወጣው ህግ በአግባቡ እየተተገበረ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።

ባለስልጣኑ የተኪ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችል የውይይት መድረክ ከአምራቾች ጋር እያካሄደ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ከተማ ብክለት ከሚያስከትሉ የፕላስቲክ አይነቶች መካከል የፕላስቲክ ከረጢቶች (ፌስታል) 46 በመቶውን እንደሚይዙ በመድረክ ላይ ተገልጿል።

የውሃ እና ለስላሳ መጠጥ ጠርሙሶች 34 በመቶ፣ የቤት ዕቃዎች 13 በመቶ እንዲሁም ሌሎች ምርቶች 4 በመቶ የብክለት መጠን እንደሚያስከትሉም ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ዲሪባ፣ አንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮች ላይ የወጣው ህግ በአግባቡ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ ተኪ ምርት አምራቾች ምርቶችን በስፋት እንዲያመርቱ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንሚያደርግም ጠቁመዋል።

ተኪ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉን የጠቆሙት ኃላፊው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

አንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ሁሉም የፕላስቲክ ከረጢቶችን ማምረትም ሆነ አገልግሎት ላይ ማዋል በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን ዜጎች መረዳት እንዳለባቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ነዋሪው እያሳየ ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ተጠይቋል።

በሀብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review