AMN – የካቲት 10/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ የተከናወኑ የኮሪደር እና ሌሎች የልማት ሥራዎች በመዲናዋ በተከናወኑ አሁጉር እና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ስኬታማነት የላቀ አስተዋፅዖ አበርክተዋል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ገልጸዋል።
አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ከሰሞኑ በመዲናዋ የተካሄዱ 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ፣ 2ኛው የጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ እና 48ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚ ምክርቤት ጉባኤ መጠናቀቅን አስመልከወተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በጉባኤዎቹ ከ20 ሺህ በላይ እንግዶች መሳተፋቸውን የገለጹት አምባሳደሩ፣ የኢትዮጵያን ገጽታ በሚያጎላ መልኩ መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በጉባኤው የመጡ እንግዶችን ከአቀባበል ጀምሮ ወደ ሀገራቸው እስኪመለሱ ባለው ሂደት፣ የኢትዮጵያን ባህልና እሴትን በሚገልጽና የኢትዮጵያን ገጽታ በሚያጎለብት መልኩ መከናወኑንም ተናግረዋል።
ከዲፕሎማሲም አንጻር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የሀገር መሪዎች የኢትዮጵያን ጥቅም ማእከል ያደረጉ የተናጥልና የባለብዙ ወገን የጎንዮሽ ውይይቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።
በጉባኤው ከ1 ሺህ 225 በላይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን መሳተፋቸውን የጠቆሙት ሚኒስትር ዲኤታው፣ ይህም የሀገርን ገጽታ ለመገንባት አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።
በጉባኤዎቹ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን የማስተናገድ አቅሟን ማሳየቷንና ለዚህም በአዲስ አበበ የተከናወኑ መሰረተ ልማቶች ለጉባኤው ስኬታመነት ትልቅ አበርክቶ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።
የተለያዩ ሀገራት መሪዎችም በመዲናዋ በተከናወኑ የልማት ስራዎች እንደተደመሙ በመግለፅ፣ ለጉብኝት እና ልምድ ለመቀመር ተመልሰው የመምጣት ፍላጎት ማሳየታቸውን አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ገልጸዋል።
በሄኖክ ዘነበ