ኢትዮጵያ ከፍተኛ የጎብኝዎች እድገት ካስመዘገቡት ሐገራት መካከል አንዷ ሆነች

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከፍተኛ የጎብኝዎች እድገት ካስመዘገቡት ሐገራት መካከል አንዷ ሆነች

AMN – የካቲት 10/ 2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በጎብኚዎች መዳረሻነት 15 በመቶ እድገት በማስመዝገብ፣ ከፍተኛ እድገት ካስመዘገቡ ሐገራት ተርታ ተቀምጣለች፡፡

የአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ከገባ ሁለተኛ ወሩ ላይ ሲሆን በዚህ አመት ቱሪዝም ከፍተኛ እመርታ እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡

እ.ኤ.አ በ2025 የዓለም የቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት የታየበት አመት ሲሆን በዘርፉ ኢትዮጵያና በደቡብ እስያ የምትገኘው ቡታን መዳረሻዎች በልዩ ክስተትነት ተመዝግበዋል፡፡

ቢቢሲ የተመድ መረጃን ጠቅሶ እንዳሰፈረው ከ1.5 ቢሊየን ጎብኚዎች በላይ እ.ኤ.አ 2025 በዓለም ዙሪያ ተጉዘዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተጠቀሰው ዓመት በዓለም አቀፍ ጎብኚዎች 15 በመቶ እድገት ማስመዝገቧን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ ይህም እንደ ተመድ የዓለም ቱሪዝም ባሮሜትር መረጃ፣ ለአፍሪካ የዘርፉ ዕድገት 8 በመቶ ድርሻ በማዋጣት ጠንካራው ቀጠናዊ እድገት እንዳደረገው ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ተደረሽነቷን በማሳደግ እና የተጓዦችን መተማመን በማሻሻል ይፋ የተደረገው “ኢትዮጵያን ይጎብኙ” መርሐ ግብር ለውጥ ማውምጣቱን ነው ዘገባው ያመላከተው፡፡

የአዳዲስ ሆቴሎች መገንባና የአገልግሎት መዘመን የጉብኚዎች ፍላጎት እንዲያድግ እንዳስቻለም ተጠቅሷል፡፡

የጉዞ ወኪል ድርጅት የሆነው “ኒው ፓዝ ኤክስፔዲሽንስ” መስራች ሳላስ ጉቬራ ኢትዮጵያ ባደረገቻቸው ማሻሻያዎች የተነሳ ቋሚ ደንበኞቻቸው ጉዞ ለማድረግ ፍላጎታቸው ማደጉን ለቢቢሲ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ኒው ፓዝ ኤክስፔዲሽንስ የመጀመሪያ ማዳረሻ እንደነበረች በመጥቀስ ከወጣት ተጓዦች የካምፕ ጉዞ ፍላጎቶች እያደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

የቲምቡክቱ ጉዞ ወኪል ሥራ አስፈጻሚ ጆኒ ፕሪንስ በዚህ ዓመት ከ20 በላይ የትምህርት ቤት ቡድኖች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ቀጠሮ እንዳሲያዙዋቸው ነው ለቢቢሲ የተናገሩት፡፡

ይህ በተያዘው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ያለውን የጉዞ ፍላጎት የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

ሳላስ ጉቬራ ኢትዮጵያ አርኪዎሎጂ፣ አንትሮፖሎጂ እና ተፍጥሯዊ ታሪክ ለመገንዘብ በዓለም እጅግ ባለጸጋ ከሆኑት ሐገራት አንዷ ናት ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ተመድ ባወጣው ሪፖርት ብራዚል 37 በመቶ፣ ቡታን 30 በመቶ፣ ግብጽ 20 መቶ እድገት ያስመዘገቡ ሐገራት ናቸው፡፡ ትንሸዋ ሲሺየልስ የ13 በመቶ እድገት አስመዝግባለች፡፡

ይህ ዕድገት በዚህ ዓመትም የበለጠ እንደሚሆን ነው ከተጓዦች ፍላጎት አንጻር የሚጠበቀው፡፡

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review