የብጉር ጠባሳን ከማከም ብጉሩን ራሱን ቀድሞ ማከም ይቀላል

You are currently viewing የብጉር ጠባሳን ከማከም ብጉሩን ራሱን ቀድሞ ማከም ይቀላል
  • Post category:ጤና

AMN የካቲት 10/2018 ዓ.ም

ብጉር (Acne Vulgaris) በብዛት በፊታችንና በሰውነታችን ላይ የሚወጣ የቆዳ በሽታ ሲሆን፣ በአግባቡ ካልታከመ ዘላቂ የቆዳ ጠባሳ ሊያስከትል ይችላል።

ብዙዎች ብጉርን እንደ ተራ የቆዳ ችግር ቢቆጥሩትም፣ እንደየደረጃው የተለያየ የህክምና ክትትል የሚሻ የጤና እክል መሆኑን በአለርት ሆስፒታል የቆዳ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ጽዮን ተስፋዬ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ አብራርተዋል።

ብጉር ከጥቁር ነጥብ እስከ ከባድ የፊት እብጠት የሚደርስ ደረጃዎች አሉት።

ዶክተር ጽዮን እንደገለጹት፣ የብጉር ህክምና የሚወሰነው እንደ ብጉሩ ብዛትና አይነት በሶስት ዋና ዋና ደረጃዎች ተከፍሎ ነው ይላሉ ።

አነስተኛ ደረጃ የሚባሉት፦ በቁጥር ከ20 በታች የሆኑ፣ በብዛት ፊት ላይ ብቻ የሚወጡና ደቃቅ የሆኑ ነጭ (Whiteheads) እና ጥቁር (Blackheads) ነጥቦችን ያካትታል።

መካከለኛ ደረጃ የሚባሉት፦ በቁጥር ከ20 እስከ 50 የሚደርሱ፣ በፊትም ሆነ በጀርባ ላይ የሚወጡና ከርቀት በግልጽ የሚታዩ ናቸው።

ከፍተኛ ደረጃ የሚባሉት ደግሞ፦ በቁጥር ከመቶ በላይ የሚሆኑ፣ ትላልቅ እብጠቶች (Cystic/Nodular) ያሉባቸውና ለከፍተኛ የቆዳ ጠባሳ የሚያጋልጡ ናቸው።

የቤት ውስጥ መከላከያ መንገዶች

ለአነስተኛ የብጉር ችግሮች የሚከተሉትን የጥንቃቄ እርምጃዎች በቤት ደረጃ መተግበር እንደሚቻል ዶክተር ጽዮን ያስረዳሉ።

ትክክለኛ ሳሙና መምረጥ፦ እንደ ቤንዞይል ፔሮክሳይድ (Benzoyl Peroxide) ወይም ሳሊሲሊክ አሲድ (Salicylic Acid) ያሉ ንጥረ ነገሮችን የያዙ የፊት መታጠቢያዎችን መጠቀም።

ማለስለሻ (Moisturizer) መጠቀም፦ የሰዉነት ቆዳ ወዝ ስላለው ብቻ ማለስለሻ መተው የለብንም፤ በተለይ ኒያሲናማይድ (Niacinamide) ያላቸው ማለስለሻዎች የቆዳን ወዝ ለማመጣጠን ይረዳሉ።

ንጽሕናን መጠበቅ፦ በመኝታ ወቅት የሚያገለግሉ እንደ ትራስ ልብስና ፎጣ ያሉትን በየጊዜው ማጠብ።

ለቆዳ አይነት የሚስማማ (Oil-free) የፀሐይ መከላከያ መጠቀም።

የህክምና አማራጮች

ብጉሩ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰ የግድ የህክምና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል የሚሉት ዶ/ር ጺዮን

የቫይታሚን ኤ ዝርያ ያላቸው (Retinoids) ወይም ባክቴሪያን የሚከላከሉ የሚቀቡ መድሃኒቶች፤ ለከፍተኛ ብጉር የሚታዘዙ የሚዋጡ የአንቲባዮቲክ መድሃኒቶች ወይም የቫይታሚን ኤ እንክብሎች (በደም ምርመራ ታግዞ የሚታዘዙ) ይሆናል ብለዋል።

ብጉርን ጠባሳ ሳይተው ቀድሞ መታከም የተሻለ መሆኑን አጽኖት የሰጡት ዶክተሯ የብጉር ጠባሳን ከመታከም ብጉርን ራሱን መታከም ይቀላል ሲሉ አሳስበዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review