AMN- የካቲት 10/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ከአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመቀናጀት፣ አዲስ የመንጃ ፈቃድ ለሚያወጡ እና እድሳት ለሚያደርጉ ሰዎች የጤና ምርመራ አገልግሎት በየክፍለ ከተማው በሚገኙ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የጤና ባለሙያችን በመመደብ አገልግሎቱን መስጠት ጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ፣ ለመንጃ ፈቃድ የጤና ምርመራ አገልግሎት የሚፈልጉ ተገልጋዮች ወደ ጤና ጣቢያ ሳይመጡ በየክፍለ ከተማው በሚገኙ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች እና በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲያገኙ ባለሙያዎችን በመመደብ መስራት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደሳለኝ ተረፈ ለመንጃ ፈቃድ የጤና ምርመራ አገልግሎቱን በአንድ ማዕከል መሰጠቱ የተገልጋዩን ህብረተሰብ እንግልት በመቀነስ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተለያዩ አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል በመቀየር እየተሰጡ መሆኑን አንስተው፣ ዛሬ የተጀመረው የመንጃ ፈቃድ የጤና ምርመራ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከልም ያግዛል ብለዋል።
ተገልጋዮች በበኩላቸው፣ ከዚህ ከቀደም የመንጃ ፈቃድ የሜዲካል ምርመራ አገልግሎት ለማግኘት አላስፈላጊ ምልልሶችን ያደርጉ እንደነበርና አሁን ወደ አንድ ማዕከል መግባቱ እንግልትና አላስፈላጊ ወጪን እንደሚያስቀርላቸው ተናግረዋል፡፡
በሄለን ጀንበሬ