AMN – የካቲት 11/2018 ዓ.ም
ኦቲዝም በሕፃናት የዕድገት ሂደት ላይ የሚከሰት ውስብስብ የአንጎል እክል ሲሆን፣ መንስኤውም በዋነኝነት በዘረመል እና በአካባቢያዊ ሁኔታዎች መካከል በሚኖር መስተጋብር የሚፈጠር እንደሆነ የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአእምሮ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር መክተው ከበደ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፣ የተወሰኑ የዘር ውርሶች ወይም ዘረመል ለኦቲዝም መከሰት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።
ከዚህም በተጨማሪ እናት በእርግዝና ወቅት የምትወስዳቸው አንዳንድ መድኃኒቶች፣ ለከፍተኛ ብክለት መጋለጥ ወይም ሕፃናት ያለ ጊዜያቸው መወለድ ለሁኔታው መከሰት እንደ ተጨማሪ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ ብለዋል።

ዶክተር መክተው እንደሚሉት፣ ምንም እንኳን ኦቲዝምን አስቀድሞ ሙሉ በሙሉ መከላከል የሚያስችል የተረጋገጠ የሕክምና ዘዴ ባይኖርም፣ በእርግዝና ወቅት የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ግን ተጋላጭነትን በእጅጉ ለመቀነስ ይረዳሉ።
እናቶች ቅድመ ወሊድ የሕክምና ክትትልን በአግባቡ ማድረግ፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብና እንደ ፎሊክ አሲድ ያሉ ቫይታሚኖችን መውሰድ እንደሚኖርባቸውም ምክር ለግሰዋል።
በተጨማሪም በእርግዝና ወቅት ከአልኮል መጠጥ፣ ከሲጋራ ጭስና ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ከሚወሰዱ መድኃኒቶች መራቅ ለፅንሱ ጤናማ የአንጎል ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ ጥንቃቄዎች ሕፃኑ ወደፊት ሊያጋጥሙት የሚችሉ የዕድገት እክሎችን ለመቀነስ የጎላ ሚና ይጫወታሉ ሲሉም አስረድተዋል። ሕፃኑ ከተወለደ በኋላም ቢሆን ወላጆች ከፍተኛ ጥንቃቄና ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

አንድ ሕፃን የንግግር መዘግየት ካሳየ፣ ከሰዎች ጋር አይን ለአይን ለመመልከት ከተቸገረ ወይም ለብቻው መሆንን የሚያዘወትር ከሆነ ወዲያውኑ ወደ ሕክምና ተቋም በመውሰድ ባለሙያ ማማከር አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኦቲዝም ቀደም ብሎ በምርመራ ከታወቀ ሕፃኑ የንግግርና የባህሪ ማስተካከያ ሕክምናዎችን በማግኘት ራሱን እንዲችል መርዳት እንደሚገባም ዶ/ር መክተው አስረድተዋል።
ከሁሉ በላይ ግን ኦቲዝም ያለባቸው ሕፃናት ከቤተሰብና ከማህበረሰቡ የሚሰጣቸው ልዩ ፍቅር፣ ትዕግስትና ድጋፍ በሕይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ዋነኛው መሣሪያ መሆኑንም ከበደ አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸው