AMN – የካቲት 11/2018 ዓ.ም
በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ አስደናቂ የሆነ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ላይ የምትገኘው ቱርክዬ፣ በብሔራዊ ስትራቴጂዎቿ አማካኝነት በዓለም አቀፍ የፈጠራ ተወዳዳሪነቷን እያረጋገጠች ትገኛለች።
በአውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ የጦር ድሮኖቿን ውጤታማነት በማሳየት የዓለምን ቀልብ የሳበችው ሀገሪቱ፣ አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን፣ የሴሚኮንዳክተር ቺፖችን እና ዘመናዊ የፊንቴክ (FinTech) መፍትሄዎችን በሀገር በቀል እውቀት በማምረት የቴክኖሎጂ ልዕለ-ኃያል ለመሆን እየተንደረደረች ነው።
እ.ኤ.አ ከ2011 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ የፈጠራ አመልካች ደረጃዋን ከ65ኛ ወደ 43ኛ ያደገችው ቱርክዬ፣ ለደረሰችበት የቴክኖሎጂ ምጥቀት ማሳያ የሆኑ ዋና ዋና ውጤቶች የሚከተሉት ናቸው፦
የቱርክዬ የመከላከያ ኢንዱስትሪ በአሁኑ ወቅት ከዓለም ቀዳሚ ከሚባሉ ሀገራት ተርታ ተሰልፏል።
እንደ ባይራክታር ቲቢ 2 (Bayraktar TB2) አይነት ድሮኖች በጦር ሜዳ ብቃታቸው የተመሰከረላቸው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ30 በላይ ሀገራት ተፈላጊ መሆን ችለዋል።
ቱርክዬ ቀደም ሲል ከውጭ ሀገራት የምታገኛቸው ካሜራዎችና ሞተሮች ሲታገዱባት፣ የራሷን ቴክኖሎጂ በመስራት ሙሉ በሙሉ ራሷን ችላለች።
አብዛኞቹ መሣሪያዎቿ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የሚታገዙ በመሆናቸው፣ በራሳቸው ውሳኔ የመስጠትና ኢላማን የመለየት ብቃት አላቸው።
ቱርክዬ የራሷን ብሔራዊ የኤሌክትሪክ መኪና ብራንድ በመፍጠር ወደ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ጉልበት ገብታለች።
ለአብነትም ቶግ (TOGG) የተሰኘውና ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰራው የቱርክዬ የመጀመሪያው መኪና ዘመናዊ ቴክኖሎጂንና ምቾትን አጣምሮ የያዘ ነው።
በተጨማሪም ለኤሌክትሪክ መኪናዎች የሚሆኑ የሊቲየም ባትሪዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ሰፊ ኢንቨስትመንት እያደረገች ትገኛለች።
ቱርክዬ በጣም የላቀና ፈጣን የባንክ ሥርዓት ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት፤ እንደ Getir (ፈጣን የዕቃ ማድረሻ) ያሉ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠሩ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መነሻቸው ቱርክዬ እንደሆነ ይነገርላቸዋል።
የቱርክዬ የቴክኖሎጂ ስኬት ምስጢር “ብሔራዊ ቴክኖሎጂ” በሚል መሪ ሀሳብ በምርምርና ልማት ላይ በሰፊው መስራቷ ነው።
ለዚህ ተግባር ዓመታዊ የምርምር ወጪ 12 ቢሊየን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ ከ270 ሺህ በላይ ባለሙያዎች ተሰማርተዋል።
እ.ኤ.አ በ2030 የሚጠናቀቀው የ30 ቢሊየን ዶላር ግዙፍ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም እንደ ሴሚኮንዳክተሮች እና ዳታ ሴንተሮች ባሉ ቁልፍ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።
የቲ 3 ፋውንዴሽን ወጣቶች የቴክኖሎጂ ክህሎት እንዲቀስሙ “ዴንያፕ” (Deneyap) የተባሉ ማዕከላትን በመፍጠር፣ ለወደፊቱ የዲጂታል ፍላጎት ብቁ የሰው ኃይል እያዘጋጀ ይገኛል።
በአጠቃላይ የቱርክዬ ተሞክሮ የሚያሳየው ከውጭ ጥገኝነት በመውጣት፣ በሀገር በቀል ዕውቀትና ምርት ላይ በማተኮር እንዴት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻል ነው።
ይህ ስኬት የራሳቸውን የቴክኖሎጂ አሻራ ለማሳረፍ ለሚጥሩ ሌሎች ታዳጊ ሀገራት ትልቅ ማሳያ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
በአስማረ መኮንን