AMN- የካቲት 11/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ እየተመዘገበ ያለው ፈጣንና ጥራት ያለው ለውጥ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን የኬንያ የፓርላማ አባል ጁኔት መሀመድ ገለጹ።
የፓርላማ አባሉ በከተማዋ ተገኝተው የታዘቡትን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ አዲሷ ዱባይ ናት በማለት በከተማዋ የመጣውን የልማት ለውጥ በምስክርነት አረጋግጠዋል።

አዲስ አበባ ከተማ እያስመዘገበችው ያለው ፈጣን እድገት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአዲሷ አፍሪካ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
የከተማዋ እድገት በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አዎንታዊ መሆኑና ማህበረሰቡን ይበልጥ እንደሚያቀራርብ አመላክተዋል።
በተጨማሪም ኬንያም ከኢትዮጵያና ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለውን የመንገድ ልማትና የንግድ ትስስር ለማጠናከር በትኩረት እየሰራች መሆኗን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ መሆኗን የጠቀሱት የፓርላማ አባሉ፣ ኬንያም ከዚህ የኃይል አቅርቦት ትልቅ ተጠቃሚ መሆኗን ገልጸዋል።
የፓርላማ አባሉ አክለውም፤ በአዲስ አበባ ከተማ የታየው የጥራትና የፍጥነት ለውጥ ወደ እውነተኛ ለውጥ ለመሻገር የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን መሆኑን ጠቁመው፤ ሀገራት እርስ በእርስ በመማማር የቀጠናውን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኬንያ ኤምባሲ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በመሰረተ ልማትና በኢኮኖሚ ዘርፎች ይበልጥ እየተጠናከረ ይገኛል።
በቶለሳ መብራቴ