አዲስ አበባ ከሶስቱ ጉባዔዎች ምን አተረፈች?

You are currently viewing አዲስ አበባ ከሶስቱ ጉባዔዎች ምን አተረፈች?

AMN – የካቲት 11/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በቅርቡ ያስተናገደቻቸው የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባዔ፥ 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 2ኛው የኢጣሊያ-አፍሪካ ጉባዔ፣ የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ አቅም ከማሳደግ ባለፈ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ረገድ ትልቅ ድል ያስመዘገቡ መሆናቸውን የሕግ ምሁርና የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ተንታኝ አቶ ማሩ አብዲ ገልጸዋል።

ባለሙያው ለኤ ኤም ኤን በሰጡት ትንታኔ፣ አዲስ አበባ እንግዶቿን የተቀበለችበት ሁኔታ ከተማዋ ለኅብረቱ አትመጥንም የሚሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በተግባር የሰበረና የከተማዋን ገጽታ የገነባ መሆኑን አስረድተዋል።

ጉባዔው በሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ሀገር እንግዶችን፣ መሪዎችን እና ዲፕሎማቶችን ወደ አዲስ አበባ ስቧል። ይህ ደግሞ ቀጥተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘቱ በላይ የተለያዩ ዘርፎችን ጠቅሟል፡፡

በከተማዋ የሚገኙ ከፍተኛ የኮከብ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተይዘው ሰንብተዋል። የአየር መንገድ፣ የኪራይ መኪናዎች እና የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል አግኝተዋል።

ጉባዔዎቹ ኢትዮጵያ ያሏት የቱሪስት መዳረሻዎች እና ለቆይታ ምቹ የሆኑ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች ለዓለም ምስክርነት የሰጡበት ነው። ይህ ዕድገት የቱሪዝም ሴክተሩን ወደ ሌላ ምዕራፍ የሚያሸጋግርና ለዘርፉ ሠራተኞችም ትልቅ የቤት ሥራና ተነሳሽነት የፈጠረ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ባሕላዊ ዕሴትና ማንነት በመጠቀም በዲፕሎማሲው ረገድ ውጤታማ መሆኗን አቶ ማሩ ገልጸዋል። አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና መሆኗን በድጋሚ ማረጋገጧ፣ በሀገሪቱ ላይ የነበረውን ያልተረጋጋች ሀገር የሚል የተሳሳተ ገጽታ ቀይሮታል።

ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በሀገሪቱ ሰላም ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያሳድጉና ለወደፊት ኢንቨስትመንት እንዲነሳሱ መንገድ ከፍቷል።
የአፍሪካና የጣሊያ መሪዎች የዲፕሎማሲ ፕሮቶኮሎችን ትተው አዲስ አበባን እንደ ቤታቸው እንዲሰማቸው መደረጉ፣ በሀገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት ይበልጥ የሚያጠናክር የዲፕሎማሲ አቅም መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ጉባዔውን በአዲስ አበባ እንዲካሔድ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓ፣ አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን እንድታረጋግጥ አስችሏታል። ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጉዳይ ላይ ያላትን ፍላጎትና ጥያቄ ለመሪዎቹ በማስረዳት በጎ ምላሽ ያገኘችበት መሆኑንም አቶ ማሩ አብራርተዋል፡፡
ጉባዔው ኢትዮጵያ ስለ ሕዳሴ ግድብ ያላትን አቋም ለመሪዎች በቅርበት ለማስረዳት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።

የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሁሉም አፍሪካዊያን ኩራት መሆኑ በመድረኩ መረጋገጡ ለሀገሪቱ ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ክብርን አጎናጽፏል ብለዋል።

ከጉባዔው ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከበርካታ የአፍሪካ መሪዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን አድርገዋል። በተለይ ከደቡብ ሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ከቡሩንዲ፣ ከናሚቢያ፣ ከኮትዲቯር፣ ከጋና ከቦትስዋና፣ ኬንያ እና ሌሎች ሀገራት ጋር ያለውን ስልታዊ ትብብር ለማጠናከር ረድቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓለም ዓቀፍ ለዘላቂ ልማት መፍትሔዎች አውታረ መረብ (SDSN) ፕሬዝዳንት ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ጋር ሰፋፊ ውይይቶችን አካሒደዋል፡፡

አዲስ አበባ ያስተናገደቻቸው እነዚህ ጉባዔዎች ኢትዮጵያ በአሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን ወሳኝ ሚና ያረጋገጡና በውጤት የታጀቡ መሆናቸውን አቶ ማሩ አብዲ ገልጸዋል።

አቶ ማሩ አንዳሉት ሕዝቡና መንግስት በቅንጅት የሠሩት ሥራ ለቀጣይ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች መዲናዋን ይበልጥ ተመራጭ እንደሚያደርጋት አረጋግጠዋል።

በቶሌሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review