AMN – የካቲት 11/2018 ዓ.ም
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ ውስጥ በጣሊያን ፋሽስት ወራሪዎች በኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ በኢትዮጵያ የታሪክ መዝገብ ውስጥ ከአሳዛኝ ክስተቶች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመው ይሄው ጭፍጨፋ በጣሊያን አገዛዝ ተወካይ ላይ የቦምብ ጥቃት በሁለት ወጣት ኢትዮጵያዊያን በሞገስ አስገዶም እና በአብርሃም ደቦጭ መደረጉን ተከትሎ ነው።
ሁለቱም በወጣትነታቸው የነፃነት ፍቅር የተነሳ በጣሊያን ወረራ ላይ ተቃውሞ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ።
በዚያ ቀን በተዘጋጀው የህዝብ ስብሰባ ላይ የጣሊያን አስተዳደር ለህዝብ ዳቦና ገንዘብ ለማከፊፈል በተሰበሰቡበት ወቅት፣ ሞገስና አብርሃ በተዘጋጀ እና በተደራጀ መንገድ ወደ መድረኩ ቀርበው ቦምብ ጣሉ።

የጣሊያን ፋሽስት አስተዳደር የቦምብ ጥቃቱን እንደ ምክንያት በመጠቀም በኢትዮጵያዊያን ላይ የከፋ የበቀል እርምጃ መውሰድ ጀመረ።
ጥቃቱ የአገዛዙን መሪ ህይወት ባያጠፋም ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ብዙ የጣሊያን ባለስልጣኖችን አቆሰለ።
ጥቃቱን ከፈጸሙ በኋላ ሞገስና አብርሃም ከአዲስ አበባ ለመሸሽ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ አቅጣጫ ተጓዙ። ነገር ግን በጣሊያን ኃይሎች ተገድለዋል ተብሎ ይታመናል። ታሪካቸው በኢትዮጵያ የነፃነት ተጋድሎ ውስጥ የጀግናነት ምሳሌ ሆኖ እስከዛሬ ድረስ ይጠቀሳል።
ዛሬ ሁለቱም እንደ ብሔራዊ ጀግኖች ይታሰባሉ፤ የፈጸሙት ጀብድ በኢትዮጵያ የተቃውሞ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ምልክት ሆኖ ተመዝግቧል።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመው ጭፍጨፋ በከተማው ውስጥ ብቻ አልተገደበም፤ በኋላ በአገር አቀፍ ደረጃ የተስፋፋ ንጹሐንን የሞትና የጉዳት ሰለባ አደረገ።
ከጥቃቱ በኋላ የጣሊያን ወታደሮችና ተባባሪዎቻቸው በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ለብዙ ቀናት የቆየ አስከፊ የበቀል ዘመቻ ጀመሩ።

በከተማው ውስጥ የተገኙ ንጹሐን ዜጎች በዘፈቀደ ተገደሉ፤ ብዙ ቤቶች ተቃጠሉ፤ ንብረቶች ተዘረፉ።
ብዙ ሰዎች በቡድን ተይዘው ከከተማ ውጭ ተወስደው ተገድለዋል ተብሎም ይገምታል። የተጠረጠሩ መሪዎች፣ ተማሪዎች እና ተቃዋሚዎች በተለይ የጭፍጨፋው ሰለባ ሆኑ።
ትክክለኛው የሞት ቁጥር እስከዛሬ በግልጽ ባይታወቅም የተለያዩ የታሪክ ምንጮች ከ20ሺ በላይ ሰዎች እንደተገደሉ ይገልጻሉ፣ አንዳንዶች ግን ቁጥሩ እስከ 30ሺ ሊደርስ ይችላል ይላሉ።
ከከተማው ውጭም በተከታታይ ጊዜያት ተጨማሪ ግድያዎች መፈጸማቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ይህ ክስተት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ፍርሃት ቢፈጥርም የነፃነት ትግሉን ማቆም አልቻለም፤ በተቃራኒው ትግሉ እንዲጠናከር አድርጓል።
በብዙ አካባቢዎች የተጠረጠሩ የነፃነት ተጋዳዮች፣ መካከለኛ መሪዎች፣ መነኮሳትና ምሁራን በብዛት ተገደሉ።
በተለይ በደብረ ሊባኖስ ገዳም የተፈጸመው ጭፍጨፋ ከአሳዛኝ ክስተቶች አንዱ ነው።

የጣሊያን ኃይሎች ገዳሙ በቦምብ ጥቃቱ የተሳተፉ ሰዎችን እንደሚያግዝ በመጠርጠር መነኮሳትንና ካህናትን በብዛት ገደሉ። የተገደሉት ቁጥር ከ1ሺ በላይ መሆኑ በታሪክ ምንጮች ይገልጻል። ይህ ጭፍጨፋ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ታሪክ ውስጥ ትልቅ የህዝብ ጉዳት አስከትሏል።
ይህ የግፍ ዘመቻ የኢትዮጵያዊያንን መንፈስ ማቆም አልቻለም። በተቃራኒው የነፃነት ትግሉ በብዙ አካባቢዎች ተጠናከረ፤ በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከጣሊያን ወረራ ነፃ ሆነች።
የካቲት 12 ክስተት በዚህ የነፃነት ታሪክ ውስጥ የህዝብ መስዋዕትነትን የሚያሳይ ትልቅ ምልክት ሆኖ ተመዝግቧል።
ቀኑ በኢትዮጵያ የሚከበረው የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ሲሆን የተሰውትን መስዋዕትነት ለትውልድ ለማስተላለፍ በየአመቱ ይዘከራል። ይህ ቀን የነፃነት ዋጋ እና የሀገር ፍቅር ትርጉም እንዳይረሳ ያስታውሳል።
በበረከት ጌታቸው