AMN- የካቲት 11/2018 ዓ.ም
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚናትና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ቆንጂት ደበላ በዓለም ለ115ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሴቶች ቀን በመተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የዘንድሮ የዓለም የሴቶች ቀን “የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበርም የቢሮ ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ለሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ቆንጅት፣ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የሴቶችን ተጠቃሚነትና ማህበራዊ ተሳትፎ ያሳደጉ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ውጤት ተመዝግቧል ያሉት ኃላፊዋ፣ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ሴቶች በቁልፍ ውሳኔ ሰጪ ቦታዎች ላይ መቀመጣቸውን በማሳያነት አንስተዋል፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ዝናሽ ከተማ፣ የዘንድሮው የዓለም የሴቶች ቀን የሴቶችን ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚያሳድጉ የተለያዩ መርሐ-ግበሮች እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡
የተለያዩ የጤና ምርመራዎችና የነፃ ህክምና መርሐ-ግብሮች በበዓሉ ወቅት እንደሚከናወኑም ወ/ሮ ዝናሽ ጠቁመዋል፡፡
ሴቶች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት እንዲሳተፉ ቢሮው የተለያዩ መርሃግብሮችን ነድፎ እየሰራ መሆኑ በመግለጫው ላይ ተመላክቷል።
በአልማዝ መኮንን