AMN – የካቲት 13/2018 ዓ.ም
ሴቶች ለሰላም ግንባታ የማይተካ ሚና እንዳላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሊድያ ግርማ ገለፁ።
“ሴት የሰላም መሰረት የልማት አውታር” በሚል መሪ ሀሳብ የአዲስ አበባ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ከሴቶች ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና ከሴት አደረጃጀት ጋር በመተባበር የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ ከ2 ሺህ በላይ ከየክፍለ ከተማው የተውጣጡ ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሊድያ ግርማ አዲስ አበባ ከተማ ታላላቅ ጉባኤዎችን የምታስተናግድ ብሎም የአፍሪካ መዲና መሆኗን ተከትሎ የሚመጡ የፀጥታ ስጋቶችን ለመመከት ሴቶች ሚናቸው ጉልህ ነው ብለዋል።
በተለይ ሴቶች በሰላም ግንባታ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ የህግ የበላይነት የሰፈነባት ህግ አክባሪ ዜጎች ያሏት ሀገርን ለመገንባት የማይተካ ሚና እንዳላቸው አንስተው፣ ኢትዮጵያ የምታከናውነው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን ሴቶች ንቁ ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ በበኩላቸው የእናቶች ተሳትፎ ለሰላም መረጋገጥ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ልዩነት በውይይት እንዲፈታ፣ ሀገራዊ ምርጫውም በተሳካ መልኩ እንዲከናወን ሴቶች ወጣቶችን እና ቤተሰብን ወደ ትክክለኛው መንገድ በመምራት ሚናቸውን እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል።
ሴቶች ለሰላም ግንባታ ባላቸው አበርክቶ ላይ ትኩረ ያደረገ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
በቤተልሔም አየነው